የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ አረፉ

የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ አረፉ

የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ቫቲካን አስታውቋል። 

“ዛሬ ጠዋት 1:35 ላይ የሮማው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ወደ አባታቸው ቤት ተመልሰዎል።መላ ህይወታቸውን ለጌታ እና ለቤተክርስቲያን አገልግሎት የሰዉ ነበሩ።” በማለት ካርዲናል ኬቨን ፌሬል፣ የቫቲካን ካሜርንጎ ተናግረዋል።

“የወንጌልን እሴት በታማኝነት፣ በጀግንነት፣ እና በዓለም አቀፋዊ ፍቅር እንድንኖር አስተምረውናል፤ በተለይ ለተቸገሩና ለተገፉ እንድንቆም።” ሲሉም አክለዋል።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ህይወት ያለፈው፤ ትላንትና እሁድ ዕለት በተከበረው የትንሳዔ በዓል በቅዱስ ጴጥሮስ ለተሰበሰበው ምዕመን በአካል ተገኝተው የበዓል መልዕክት ባስተላለፉ ማግስት ነው። ከደቡብ አሜሪካ የተሾሙ የመጀመርያው ሊቀ ጳጰስ የሆኑት ፖፕ ፍራንሲስ ከመተንፈሻ አካላት ህመም ጋር በተያያዘ የሕክምና ክትትል ሲደረግላቸው ነበር። ከወር በፊት ነበር ለአምስት ሳምንታት ከቆዩበት ሆስፒታል የወጡት። ሐኪሞቻቸው ለሁለት ወር ያህል እንዲያርፉ ቢነግሯቸውም፣ ምእመናንን ሰላም ለማለት ወደ አደባባይ መምጣታቸውን ቀጥለው ነበር ።

የዓለም መሪዎች ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው። የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን “ትህትና የተሞላባቸው ሰው” በማለት ገልፀዋቸዋል። የደቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዲክ ስሆፍ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ “በሁሉም መስክ የሕዝብ ሰው” ነበሩ ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሀዘናቸውን ከገለፁት መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው።

ትላንት ከዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄ ዲ ቫንስ ጋር ለአጭር ጊዜ ተገናኝተው ነበር። ይህ የውይይት ዓላማም በትራምፕ አስተዳደርና በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማብረድ ያለመ ነበር። ፖፕ ፍራንሲስ ከትራምፕ ጋር በብዙ ጉዳዮች ላይ የሚቃራኑ አቋሞች ነው የነበራቸው ሲሆን በተለይ የትራምፕን የፀረ-ስደተኛ አቋም አጥብቀው ይቃወሙ ነበር።  

ቀዳሚያቸው ፖፕ ቤኔዲክት 16ኛ መንበራቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ነበር ፖፕ ፍራንሲስ በአውሮፓውያኑ 2013 የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሩ የተመረጡት።

Share this post

Post Comment