“ሕግ መንግሥቱን ለማስጠበቅ፣ ለመመከት እና ለመከላከል አቅሜ በፈቀደው ሁሉ ኃላፊነቴን በታማኝነት ለመወጣት ቃል እገባለሁ። ለዚህም ፈጣሪ ይርዳኝ!” በማለት ቃለ መሐላቸውን የፈፀሙት 47ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገፃቸው ፈገግታ አልባ ነበር። ዋሽንግተን ውስጥ በሚገኘው በምክር ቤቱ ህንጻ “ካፒቶል ሮቶንድ” አዳራሽ በተከናወነው ሥነ ሥርዐት ላይ ልክ ኮስተር ብለው እንደተነሱት ኦፊሴላዊ ፎቶ ሁሉ ፊታቸው እንደጨፈገገ ነበር። ወደ መድረኩ ወጥተው ንግግራቸውን ሲጀምሩ ብቻ ነው ፊታቸው ትንሽ ፈታ ያለውና “የአሜሪካ ወርቃማ ዘመን” መጀመሩን ያበሰሩት።”ከዚህ ቅጽበት ጀምሮ “የአሜሪካ ውድቀት አብቅቷል” የሚል ንግግር አሰምተዋል።ከተሰናባቹና ለግማሽ ምዕተ ዓመት አገራቸውን ያገለገሉት ጆ ባይደን በተቀመጡበት።
ከስምንት ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመረጡ እንዳደረጉት ንግግር ሁሉ ለአሜሪካ ሕዝብ “ጥንካሬን” የማስመለስ አላማቸውን ገልፀዋል።የትናንቱ ንግግር ጠንከርና ጠጠር ያለ ሲሆን፤ ይህም ድንበሩን እና በሀገሪቱ በህገ ወጥ መንገድ የሚገኙ ዜጎችን በብዛት ማባረር፣ በሌሎች አገሮች ላይ አሜሪካ “የሚኖራትን ዘላቂ የበላይነት” አፅንተው ገልፀዋል። “አሜሪካ የወደቀበችበት የአራት ረጅም ዓመታት መጋረጃ ይዘጋና አዲስ የአሜሪካ ጥንካሬ እና የብልጽግና ቀን እንጀምራለን” ብለዋል። በሜክሲኮ ድንበር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሚደነግጉ ሲናገሩ ሞቅ ያለ ጭብጨባ ተደርጐላቸዋል። ትራምፕ ኃይል ለማመንጨት የሚደረግ ቁፋሮ እንደሚቀጥል (« Drill, baby, drill ») በማለት፣ ገልፍ ኦፍ ሜክሲኮ አካባቢ ገልፍ ኦፍ አሜሪካ እንደሚባል (በዚያች ቅጽበት ሂላሪ ክሊንተን ሲስቁ ተስተውለዋል) ና ፓናማ ካናልን አሜሪካ እንደምትወስድ ፤ ግዛቷንም እስከማርስ ድረስ እንደምታሰፋ ተናግረዋል።
በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ባለው ከባድ ብርድ ምክንያት የተነሳ ሥነ ሥርዐቱ ምክር ቤት ህንጻ “ካፒቶል ሮቶንድ” ስለተደረገ በርካታ ሰው ተጨናንቆ ነበር። ይህ ሥነ ሥርዓት ሮናልድ ሬገን እኤአ በ1985ዓ/ም ካደረጉት የቤት ውስጥ በአለ ሲመት ወዲህ የመጀመርያው ነው። በቃለ መሐላ ሥነ ስርዐት ላይ የቀድሞዎቹ ፕሬዝዳንቶች ቢል ክሊንተን፣ ጆርጅ ደብሊው ቡሽ እና ባራክ ኦባማ፣ ሲገኙ እንደ እስክንድርያ ኦካሲዮ ኮርቴዝ ያሉ አንዳንድ ዲሞክራሲያዊ አባላት ለመታደም ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።የቴስላና የቀድሞው ትዊተር የአሁኑ ኤክስ ባለቤት ኢላን መስክ፣ የአማዞኑ ጄፍ ቤዞስ፣የሜታው ማርክ ዘከርበርግ እና የቲክቶክ የሥራ አስፈጻሚ ሹ ዚ ቼውም ተገኝተዋል። የቻይና ምክትል ፕሬዝደንት ሃን ዤንግ፣ የጣሊያን ቀኝ አክራሪ ፓርቲና ጠቅላይ ሚንስትር ጆርጂያ መሎኒ እና የአርጀንቲናው ፕሬዝደንት ሃቪየር ሚሌ ከተጋበዙት የውጭ መሪዎች መካከል ይጠቀሳሉ።