የማዳመጥ ሃይል

የማዳመጥ ሃይል

ብዙ የማውራት አመል ያለባቸው  ሰዎች በየቦታው ሞልተዋል።በምትሄድበት ቦታ ሁሉ ታገኛቸዋለህ ። የሥራ ባልደረቦችህ ሊሆኑ ይችላሉ፤ መስርያ ቤት ውስጥ ሰኞ ጠዋት ላይ ቅዳሜና እሁድ ስላደረጉት ስለሚረባውም ስለማይረባውም  ነገር በማውራት የሚያታክቱህ።ወይም በእራት ግብዣ ላይ ሌላውን በማቋረጥ፥ እኔ ብቻ ካላወራሁ የሚሉ የሥጋ ዘመዶችህ። ድንገት እቤት መጥተው ሥራ ላይ ትሁን አትሁን ለማውቅ ሳይገዳቸው የባጥ የቋጡን የሚዘላብዱ፤ ከዚህ በፊት  የነገሩህን ነገር ደግመው የሚነግሩህ ጎረቤቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

እውነቱን ለመናገር፣ ብዙዎቻችን እንደዚያ ነን።ጥፋቱ የእኛ ብቻ አይደለም ።የምኖርበት አለም ማውራትን የሚያበረታታ ብቻ ሳይሆን ዘውትር የሚጋብዝ ነው።የእኛ ስኬታማነት የሚመዘነው በምናገኘው ትኩረት መጠን ነው።ትዊተር ላይ ምን ያህል ተከታዮች አሏችሁ? ኢንስታግራም ላይስ ምን ያህል ተከታዮች ሰበሰባችሁ? የሚሉ ጥያቄዎችን መስማት የተለመደ ነው።በየቀኑ የሚፈለፈሉ የዪቱብ ገጾች አሉ፤ ፖድካስቶችም እንደዛው።ከ 48 ሚልዮን በላይ ዝግጅቶችን ያስተላለፉ 2 ሚልዮን ፖድካስቶች እንዳሉ ከሁለት ዓመት በፊት ተዘግቦ ነበር። በቲክቶክና ፌስቡክ የጋብቻ አማካሪ፣ የፖለቲካ ተንታኝና ሃይማኖት  ሰባኪያን በየቀኑ እንደ አሸን ይፈላሉ።

በዚህ ግፊት ምክንያት፥ ዝም ብለን ትዊት ለማድረግ እንሽቀዳደማለን።ለማውራት እንጣደፋለን። በጣም የተሳካላቸውና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ግን፥ እንደዚህ አይደሉም።እዩኝ እዩኝ ከማለት ይልቅ ራሳቸውን ወደ ሗላ ይገታሉ።በሚናገሩበት ጊዜ፥ ስለሚሉት ነገር ጥንቃቄ ያደርጋሉ።አፕል የተሰኘው ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ቲም ኩክ በጭውውት ወቅት ለረጅም ደቂቃዎች ዝም ይላሉ።አልበርት አንስታይን ብቻውን መሆን የሚወድ ቁጡብ ሰው ነበር ። የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩት ሩት ባደር ጊንስበርግ በሚናገሩበት ጊዜ ቃላቶቻቸውን በጥንቃቄ የሚመርጡ ሲሆን፤ ብዙ ፋታም ይወስዱ ነበር።አንድ ነገር ይሉና የሚቀጥለውን ነገር ከመናገራቸው በፊት ጊዜ ይወስዳሉ።

ብዙዎቻችን በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነን አንሾምም ወይም የቴክኖሎጂ  ኢንዱስትሪውን የምንመራ ቢሊየነር የመሆን ዕድል ላይኖርን ይችላል።ይሁን እንጂ በየዕለቱ ትግላችን ድል መምታት እንችላለን።አዲስ መኪና ወይም ቤት መግዛት፤ የሥራ እድገት ለማግኘት፤ ወዳጆችን ለማፍራትና ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር። አፋችንን እንለጉመው።

Share this post

Post Comment