ብዙ የማውራት አመል ያለባቸው ሰዎች በየቦታው ሞልተዋል።በምትሄድበት ቦታ ሁሉ ታገኛቸዋለህ ። የሥራ ባልደረቦችህ ሊሆኑ ይችላሉ፤ መስርያ ቤት ውስጥ ሰኞ ጠዋት ላይ ቅዳሜና እሁድ ስላደረጉት ስለሚረባውም ስለማይረባውም ነገር በማውራት የሚያታክቱህ። የሥጋ ዘመዶችህ ሊሆኑ ይችላሉ፤ በእራት ግብዣ ላይ ሌላውን በማቋረጥ፥ እኔ ብቻ ካላወራሁ የሚሉ። ጎረቤቶች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ድንገት እቤት መጥተው ሥራ ላይ ትሁን አትሁን ለማውቅ ሳይገዳቸው የባጥ የቋጡን የሚዘላብዱ፤ ከዚህ በፊት የነገሩህን ነገር ደግመው የሚነግሩህ።
እውነቱን ለመናገር፣ ብዙዎቻችን እንደዚያ ነን።ጥፋቱ የእኛ ብቻ አይደለም ። የምኖርበት አለም ማውራትን የሚያበረታታ ብቻ ሳይሆን ዘውትር የሚጋብዝ ነው።የእኛ ስኬታማነት የሚመዘነው በምናገኘው ትኩረት መጠን ነው።ትዊተር ላይ ምን ያህል ተከታዮች አሏችሁ? ኢንስታግራም ላይስ ምን ያህል ተከታዮች ሰበሰባችሁ? የሚሉ ጥያቄዎችን መስማት የተለመደ ነው።በየቀኑ የሚፈለፈሉ የዪቱብ ገጾች አሉ፤ ፖድካስቶችም እንደዛው።ከ 48 ሚልዮን በላይ ዝግጅቶችን ያስተላለፉ 2 ሚልዮን ፖድካስቶች እንዳሉ ከሁለት ዓመት በፊት ተዘግቦ ነበር። በዚህ ግፊት ምክንያት፥ ዝም ብለን ትዊት ለማድረግ እንሽቀዳደማለን።ለማውራት እንጣደፋለን። በጣም የተሳካላቸውና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ግን፥ እንደዚህ አይደሉም።እዩኝ እዩኝ ከማለት ይልቅ ራሳቸውን ወደ ሗላ ይገታሉ።በሚናገሩበት ጊዜ፥ ስለሚሉት ነገር ጥንቃቄ ያደርጋሉ።አፕል የተሰኘው ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ቲም ኩክ በጭውውት ወቅት ለረጅም ደቂቃዎች ዝም ይላሉ።አልበርት አንስታይን ብቻውን መሆን የሚወድ ቁጡብ ሰው ነበር ። የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩት ሩት ባደር ጊንስበርግ በሚናገሩበት ጊዜ ቃላቶቻቸውን በጥንቃቄ የሚመርጡ ሲሆን፤ ብዙፋታም ይወስዱ ነበር።አንድ ነገር ይሉና የሚቀጥለውን ነገር ከመናገራቸው በፊት ጊዜ ይወስዳሉ።