የማዳመጥ ሃይል

የማዳመጥ ሃይል

ብዙ የማውራት አመል ያለባቸው  ሰዎች በየቦታው አሉ።በምትሄድበት ቦታ ሁሉ ታገኛቸዋለህ ። የሥራ ባልደረቦችህ ሊሆኑ ይችላሉ፤ መስርያ ቤት ውስጥ ሰኞ ጠዋት ላይ ቅዳሜና እሁድ ስላደረጉት ስለሚረባውም ስለማይረባውም  ነገር በማውራት የሚያታክቱህ። አልያም በእራት ግብዣ ላይ ሌላውን በማቋረጥ፥ እኔ ብቻ ካላወራሁ የሚሉ የሥጋ ዘመዶችህ። ድንገት እቤት መጥተው ሥራ ላይ ትሁን አትሁን ለማውቅ ሳይገዳቸው የባጥ የቋጡን የሚዘላብዱ፤ ከዚህ በፊት  የነገሩህን ነገር ደግመው የሚነግሩህ ጎረቤቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

እውነቱን ለመናገር፣ ብዙዎቻችን እንደዚያ ነን።ጥፋቱ የእኛ ብቻ አይደለም። የምኖርበት አለም ማውራትን የሚያበረታታ ብቻ ሳይሆን ዘውትር የሚጋብዝ ነው።ስኬታማነታችን የሚመዘነው ምን ያህል ትኩረትን ለመሳብ ችለናል በሚለው መጠን ነው። ትዊተር ላይ ምን ያህል ተከታዮች አሏችሁ? ኢንስታግራም ላይስ ምን ያህል ተከታዮች ሰበሰባችሁ? የሚሉ ጥያቄዎችን መስማት የተለመደ ነው።በየቀኑ የሚፈለፈሉ የዪቱብ ገጾች አሉ፤ ፖድካስቶችም እንደዛው።ከ 48 ሚልዮን በላይ ዝግጅቶችን ያስተላለፉ 2 ሚልዮን ፖድካስቶች እንዳሉ ከሁለት ዓመት በፊት ተዘግቦ ነበር። በቲክቶክና ፌስቡክ የጋብቻ አማካሪ፣ የፖለቲካ ተንታኝና ሃይማኖት  ሰባኪያን በየቀኑ እንደ አሸን ይፈላሉ።

በዚህ ግፊት ምክንያት፥ ዝም ብለን ትዊት ለማድረግ እንሽቀዳደማለን።ለማውራት እንጣደፋለን። በጣም የተሳካላቸውና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ግን፥ እንደዚህ አይደሉም።እዩኝ እዩኝ ከማለት ይልቅ ራሳቸውን ወደ ሗላ ይገታሉ።በሚናገሩበት ጊዜ፥ ስለሚሉት ነገር ጥንቃቄ ያደርጋሉ።አፕል የተሰኘው ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ቲም ኩክ በጭውውት ወቅት ለረጅም ደቂቃዎች ዝም ይላሉ።አልበርት አንስታይን ብቻውን መሆን የሚወድ ቁጡብ ሰው ነበር ። የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩት ሩት ባደር ጊንስበርግ በሚናገሩበት ጊዜ ቃላቶቻቸውን በጥንቃቄ የሚመርጡ ሲሆን፤ ብዙ ፋታም ይወስዱ ነበር።አንድ ነገር ይሉና የሚቀጥለውን ነገር ከመናገራቸው በፊት ጊዜ ይወስዳሉ።

ብዙዎቻችን በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነን አንሾምም ወይም የቴክኖሎጂ  ኢንዱስትሪውን የምንመራ ቢሊየነር የመሆን ዕድል ላይኖርን ይችላል።ይሁን እንጂ በየዕለቱ ትግላችን ድል መምታት እንችላለን።አዲስ መኪና ወይም ቤት መግዛት፤ የሥራ እድገት ለማግኘት፤ ወዳጆችን ለማፍራትና ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር። አፋችንን እንለጉመው።

በተለይ ወንዶች የማውራት አመል አለባቸው ። ምንም ነገር “ከመተርተር” አይመለሱም።በየአጋጣሚው ፍሬከርስኪ ወሬ ይደስኩራሉ። ሌላውን ያቋርጣሉ።በበኩሌ ይህ የኔ ችግር ነው። ሀይለኛ የማውራት አመል አለብኝ። ብዙ ዋጋም አስክፍሎኛል። ብዙ ማውራቴ ብቻ አይደለም፤ ደጋግሜ የማይባል ነገር ማለቴና  የምላስ ወለምታ ሰለባ መሆኔ ነው።ለራሴ ብቻ ማለት የሚገባኝን ነገር ካለምንም ይሉኝታ አደባባይ አሰጠዋለሁ። ለወሬ የፈጠንኩ ሰው መሆኔ ሥራየን አሳጥቶኛል፤ ብዙ ሚሊዮን ብርም እንደዛው።በዚህ ጊዜ ነበር፣ ከባለቤቴና ከልጆቼ ርቄ በተከራየሁት ቤት ውስጥ፣ ብቻዬን በመሆን ራሴን መገምገም የጀመርኩት። የመጠጥ ሱሰኞች የራስን መፈለግ እና ድፍረት የተሞላበት ሞራላዊ ምርመራ ብለው የሚጠሩት አይነት።የተረዳሁት ነገር ቢኖር ከመጠን በላይ ማውራቴ ሕይወቴን በብዙ መልኩ እንዴት እንዳመሳቀለው ነው።ይህም ለሁለት ጥያቄዎች መልስ ፍለጋ እንድነሳ አደርጎኛል ፤ አንዳንድ ሰዎች ለምንድን ነው ለፍላፊ የሚሆኑት፤ እንዴትስ መቀየር ይቻላል።በዚህ አጋጣሚ የኔ ልክፍት ስም እንዳለው ለመረዳት ቻልኩ። talkaholism (ቶክሊዝም ፦የአልኮል ሱሰኝነትን ለመግለፅ ከምንጠቀምበት ቃል አልኮሊዝም ላይ አልኮን በማስወገድ በምትኩ ወሬን በመጨመር ሁለት ምሁራን የፈጠሩት ቃል።) “የማውራት አመል እንደ መጠጥ ሱስ ነው።ብዙ  ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች ያላቸው የቃላት ፀጋ በሙያቸው እድገት ለማግኘት ሊረዳቸው ቢችልም  ለአፋቸው ለከት አለመኖሩ በግልም ሆነ በሥራቸው ላይ ችግር ያስከትልባቸዋል” ሲሉ የ ምዕራብ  ቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ቨርጂኒያ ሪችመንድ እና ጄምስ ማክሮስኪ ይናገራሉ።

የማውራት አመል ያለባቸው ሰዎች  (በአንዳንዶች አባባል Talkaholics) ብዙ ላለመናገር ቢሞክሩም እንዳሰቡት አይሳካላችውም።ራሳቸውን ለመግታትና አነጋገራቸውን ለመቆጠብ ቻይነት የላቸውም፡፡ ከሌላ ሰው በላይ ማውራታቸው ብቻ አይደለም፤ በተደጋጋሚ በሁሉም አጋጣሚ ዝም ብለው እንደቁራ መለፍለፋቸው ነው። ተገቢ ያልሆነ ነገር ብለው፤ በኋላ ላይ የሚቆጩበት ቢሆንም እንኳ ማውራታቸውን አያቆሙም። አመል ስለሆነባቸው።


 

ታይም መጽሔት ላይ “Talking Less Will Get You More” በሚል ርዕስ የቀረበ። 

Share this post