“የእስር ቤቱ አበሳ –
በታላቁ ቤተ መንግስት (1966—1974)” በሚል ርዕስ በአበራ ጀምበሬ ከተፃፈው መፅሐፍ ላይ የተቀነጨበ
ቶማስ ወልድ የኢትዮጲያዊ ስም ነው ወይስ የሌላ አገር ሰው? ያልተለመደ የስም አወጣጥ!! “ቶማስ” የኢትዮጲያም የሌላም አገር ሰው ስም ሊሆን ይችላል። ሥር መሠረቱም መጽሐፍ ቅዱስ ነው ።ለዚህም ነው በየትኛውም አገር ሊወጣ የሚችል ስም የሚሆነው። “ወልድ” ግን ጥሬ ዘሩ ኢትዮጲያዊ ነው። እርሱም በግዕዝ እና በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገኝ ነው። በሃይማኖት ትምህርት “ወልድ” ማለት ልጅ ማለት ሲሆን፤ ከሦስቱ ሥላሴዎች የአንደኛው፤ ሰው የሆነው አምላክ የወልድ የመጠርያ አምላካዊ ስም ነው። ለሰብአዊ ፍጡር ግን ይህ ስም የሚሰጠው ከአናባቢ ጋር ብቻ ነው።ለምሳሌ አካለ ወልድ፥ ቃለ ወልድ፥ ሀብተ ወልድ ተሰኝቶ እንጂ ብቻውን አይደለም። ስለዚህ “ቶማስ ወልድ” የፈጠራ እንጂ እውነተኛ ስም አይመስልም፤ በተለይ ለኢትዮጲያዊ። ታዲያ ለኢትዮጲያዊነቱ አስተማመኝነት የሌለው ስም በተለይ ስለኢትዮጲያ ቤተ መንግሥት የእስር ቤት አበሳ በሚያዘክር መጽሐፍ ውስጥ ምን አግባብነት አለው? የሚል ጥያቄ ይቀርብ ይሆናል።
ስመ ስያሜው አግባብነት ይኑረውም፥ አይኑረውም በዚህ ስም ለተወሰነ ጊዜ ይታወቁ ወይም ይጠሩ የነበሩ ሰው በዚህ መጽሐፍ ማዕቀፍ በኢትዮጲያ ውስጥ ምን ሚና እንደነበራቸው የሕይወት ታሪካቸው ስለሚገልፅ፤ ፍጻሜያቸውን ከሥራቸው ጋር ያገናዝቧል።
በኢትዮጲያ፥ በግብጽና በፈረንሣይ አገር የተማሩ የሕግ እና የፖለቲካል ሳይንስ ምሩቅ ናቸው ቶማስ ወልድ። በ 1928 ዓ.ም ነበር ለኢትዮጲያ ሕልውና ጠበቃ ሁነው በፓሪስ የፖለቲካዊ መድረክ ላይ ብቅ ያሉት።የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሙኤል ሆርና የፈረንሳዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፒየር ላቫል ላደረጉት የሆር-ላቫል ስምምነት የመቃወሚያ መግለጫ በማውጣት ነበር በፓሪስ የኢትዮጵያ ሌጋስዮን በፕሬስ አታሼነት መንግሥታዊ ገልጋሎትን በክፉው ጊዜ የጀመሩት።እኒህ ሰው ለኢትዮጵያ ሕልውና የሚታገሉ ሁለት ኮሚቴዎችን በፈረንሳይ አገር በማቋቋም በእነዚሁ በመታገዝ የኢትዮጵያ ዜና (Nouvelles d’Éthiopie) የሚል ጋዜጣ በመመሥረት የኢትዮጵያን አቋም ለዓለም አሳወቁ።በመንግሥታቱ ማህበር (League of Nations) የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ጸሐፊ በመሆን በፓሪስ የኢትዮጵያ ሌጋስዮን ሚኒስትር ከነበሩት ከፊታውራሪ ተክለ ሃዋርያት ዋየህ ጋር ከፓሪስ ወደ ጄኔቭ እየተመላለሱ ስለኢትዮጵያ ተሟገቱ።
በጋዜጣም በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጽመውን ደባ ለዓለም አጋለጡ፡፡ ከሚያዝያ ወር 1928 ዓ.ም ጀምሮ በፓሪስ የኢትዮጵያ ሌጋሲዮን አንደኛ ጸሐፊ በመሆን በግዚያቱ የኢትዮጵያ ሚኒስትር የነበሩት ብላቴን ጌታወልደማርያም ሲከዱ ደግሞ ከመስከረም 1929 ዓ.ም ጀምሮ በሌጋሲዮኑ በጉዳይ ፈጻሚነት ሠሩ። በአምስቱ የወረራ ዓመታት ከ አቶ መኮነን ሀብተ ወልድ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ስደተኞች መረዳጃ ማህበር በማቋቋም ስደተኞችን ሲረዱ ቆዩ፡፡ በናዚስት ጀርመን ጦር ጫሪነት የፈረንሣይ መንግሥት ወድቆ ከፓሪስ ወደ ቦርዶ ሲዘዋወር በብዙ ችግር በብስክሌት ወደዚያ ሄደው ለኢትዮጵያ ነጻነት ታገሉ፡፡የጀርመን ጦር ወደ ዚያው ሲገሰግስ ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ተገደዱ፡፡
የወጣቱ ዲፕሎማት መልክ የላቲን አሜሪካ አገሮች ሰው ያስመስላቸዋል፡፡የላቲን አሜሪካ ሰው የሚያስመስላቸው ደም ግባታቸው ፣ ቀለማቸው፣ ገፅታቸው፣ ፀጉራቸውና የአፍንጫቸው ቅርጽ ነው፡፡ ለዚህም ነው ብዙዎች የሜክሲኮ ወይም የኮሎምቢያ ተወላጅ እንደሆኑ አድርገው የሚወስዱዋቸው የነበረው።ይህም ነበር በፈረንሣይ አገር በማርሴይ ከሚገኘው የኮሎምቢያ ቆንስል ‹‹ቶማስ ወልድ›› በሚል ስም የኮሎምቢያ ሊሴ ፓሴ (ፓስፖርት) ለማውጣት የረዳቸው፡፡ የራሳቸውን ፓስፖርት በኪሳቸው ይዘው እንዳይገኙ በፓሪስ የአሜሪካ አምባሳደር በሌላ ዘዴ እንዲላክላቸው በአደራ ሰጥተው ፥ የትምህርት ቤት ጓደኛቸውን፥ ፈረንሳይቱን ፍቅረኛቸውን ማዳም ኮሌትን ተሰናብተው ማንነታቸውን ላለማሳወቅ በሌላ አገር ፓስፖርት ወደ ፖርቱጋል ሹልክ አሉ፡፡የአሜሪካን አምባሳደርም የላኩላቸውን እውነተኛውን ፓስፖርታቸውን ለማግኘት የቻሉት ሊዝበን ከተማ ሲደርሱ ነበር ፡፡ ሊዝበን ከደረሱ በኋላ የተንቀሳቀሱት በአሳሳች ስምና በኮሎምቢያ ፓስፖርት ሳይሆን ከፓሪስ በተላከላቸው በእውነተኛው ፓስፖርታቸው ነበር ፡፡
ኢትዮጵያ ከኢጣሊያ ቅኝ አገዛዝ ነፃ እንደወጣች ከነበሩበት ወደ እንግሊዝ አገር ሄደው በመርከብ የመሳፈር ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ለእንግሊዝ መንግሥት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ጥያቄአቸው ሲፈቀድላቸው በአፍሪካ ዞረው ሞምባሳ ደረሱ፤ ከዚያም በመነሳት በ1934 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቡ፡፡
በነፃነት ማግስት ቶማስ ወልድ በጽሕፈት ሚኒስቴር ውስጥ እንዲሰሩ ተመደቡ።በዚህ ጊዜ ነበር የሕግ ሐሳብና ስለኢትዮጵያን አቋም ራፖር ማቅረብ የጀመሩት፡፡ በዚህ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትርነት ሲሾሙ ነበር የሥልጣን እርካብ የረገጡት፡፡
በአፍላ ዕድሜያቸውም በሎርድ ላንግ ፎርድ መሪነት የእንግሊዝ የልዑካን ቡድን ለድርድር አዲስ አበባ ሲመጣ በኢትዮጵያ ተዋዋይ ቡድን አፈ ጉባኤነት የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ እንዲቋቋም፤ በምስራቅ አፍሪካ ሺሊንግ ፈንታ የኢትዮጵያ ብር የሀገሪቱ ህጋዊ መገበያያ እንዲሆንና በማንኛውም ረገድ የኢትዮጵያ ጥቅም በሚገባ እንዱጠበቅ በሰፊው ተከራከሩ፤ የተሳካ ውጤትም ለማስገኙት ቻሉ።
(ይቀጥላል)