የታ-ኒሂሲ ኮትስ አዲስ መጽሐፍ “መልዕክቱ”

የታ-ኒሂሲ ኮትስ አዲስ መጽሐፍ “መልዕክቱ”

የዝነኛው ናሽናል ቡክ አዋርድ አሸናፊ የሆነው አፍሪካ አሜሪካዊ ታ-ኒሂሲ ኮትስ በ2015 Between the World and Me በሚል ርዕስ ሥር ያሳተመውና በ2017 We Were Eight Years in Power (ለስምንት ዓመታት ያህል ስልጣን ላይ ነበርን) በሚል ርዕስ ያሳተመው ሌላ መጽሐፍ የባርነት አገዛዝና ‘ጂም ክሮው’ የተሰኘው ጨቋኝ ሕግ፣ዛሬም ድረስ የቀጠለው ኢፍትሐዊ ሥርዓት ያለፈውና የአሁኑን አሜሪካ ታሪክ እንዴት እንደቀረፀው ፍንትው አድርጐ ያሳያል።ግልጽና ሃያል የሆነው ብዕሩ ይህን ያለፈውን ጊዜ ሳንፈራ እንድጋፈጥና ፈወስ ለመሻት እንድንጥር ጥሪ ያቀርባል።አሁን በቅርቡ የወጣው “መልዕክቱ” (The Message) የተባለው መፅሐፉ፤ ያለፈ ጊዜ ትዝታ፣ የጉዞ ማስታወሻና የአፃፃፍ ዘዴ መርሆችን በአንድ ላይ አጣምሮ የያዘ ነው። የሴኔጋል ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ዳካር፣ የትውልድ አገሩ አሜሪካ ውስጥ የሚገኙት ኮሎምቢያ፣ ደቡብ ካሮላይናና እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ የተለያዩ ከተሞች ስላደረገው ጉብኝትና ጉዞ ይዘክራል።

Between the World and Me የተባለው መፅሐፉ በጉርምስና ዕድሜ ላይ ለሚገኘው ልጁ የተጻፈ ልብ የሚነካ ደብዳቤ ሲሆን፣ The Message “ጓዶች” ብሎ ለሚጠራቸው ለሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ የአፃፃፍ ዘዴ ተማሪዎቹ እንዲደርስ እንደ ደብዳቤ ተደርጎ የተፃፈ ነው። “ቢረፍድም ድርሻየን ለመወጣት ብቅ ብያለሁ።ይህንን ማስታወሻ በቀጥታ ለእናንተ ነው የምፅፈው።ዓለምን ለመታደግ የበኩላቸውን በማድረግ ላይ ላሉ በሁሉም ቦታ የሚገኙ ወጣት ፀሐፍትንም እያሰብኩ ቢሆንም።” በማለት ይጀምራል።ኮትስ በእያንዳንዱ ትረካ የራሱን የህይወት ልምድ ያጋራል፣ ግን ሁልጊዜ ለጸሐፊዎች ትምህርትና ምክር መለገሱን ሳይዘነጋ። ወደ አፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በሄደበት ወቅት ይህን ይላል። “ቃላቶችህ ሪትም፣ ይዘት፣ ቅርጽ፣ ስሜትን አጭቀው የያዙ ናቸው። …አንድ ጸሐፊ ከባድ መከራ የተሞላበትንና ምቾት የሌለውን ሕይወት በተሟላ መልኩ መቅረፅና ማሣያት መቻል አለበት።”

በኮትስ አባባል ጸሐፊዎች በተለይም ጥቁር ጸሐፍት የሚያዩትንና የሚያስተዉሉትን ነገር በግልጽ የሞራል መነጽር የመዘገብ ግዴታ አለባቸው፣በተለይም ማህበረሰቡ እምነታቸውን ሆነ ብሎ በሚፃረርበት ጊዜ። “ዓላማቸው የሞተ ዓለምን ማየት ለሚፈልጉ ሰዎች በሚያገለግሉ የሞቱ ቋንቋዎችና ታሪኮች ተከበናል”። በማለት ይጽፋል። በመቀጠልም “እየሸፋፈኑ የማቅረብን አካሄድ መታገል ብቻ በቂ አይደለም።በውስጣችሁ አንድ ነገር ሊኖር ይገባል። የጠራ ነገርን ለማቅረብ መጏጏት፤ ያጉጉት ሁሌም ከእናንተ ጋር ሊኖር ይገባዋል። ያንን መንገድ በመከተል፥ አፈ ታሪክና የእነሱን ታሪክ ብቻ ሳይሆን እናንተ ውስጥ ያለውንም ጭምር ትጋፈጣላችሁ።” ይላል። “

አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ ጥቁር ጸሐፍት «የባሪያ ገዥዎችን፣ ቀኝ ገዥዎችና የየተንኮለኞችን መሥፈርቶች» መከተል እንደማያስፈልጋቸው ጠቁሞ ከዚህ ይልቅ መሥፈርት አድርገው መከተል ያለባቸው አፃፃፋችውንን በማስላት የብርሃን ጥራታችውን ከፍ ማድረግ ነው። “በዚያም ብርሃን እስከ አሁን ሲነገሩን የነበሩ ታሪኮች መመርመርና መሞገት፣ ተቀብለናቸው የኖርናቸውን የፖለቲካ መስመሮች እንዴት እንደሚደገፉ ማስተዋል፣ ከዚያም እኛ ራሳችን አዳዲስ ታሪኮችን ይዘን መቅረብ።” ይገባናል ሲል ይመክራል።

ሁለተኛው ምዕራፍ የሚያተኩረው፣ አገሩ ላይ ስለተፈጠረ ጉዳይ ነው። ደራሲው በደቡብ ካሮላይና ሲሄድ፣ የትምህርት ቤቱ ቦርድ በ2015 የታተመው መጽሐፉን “Between the World and Me” ለማገድ እየተዘጋጀ ነበር፤ ምክንያቱም የተወሰኑ ተማሪዎች ሲያነቡት “ነጭ በመሆናችን እንድናፍር አድርጐናል” የሚል ስሞታ በማቅረባቸው ነው።የደራሲው ደጋፊዎች ተሠባስበው በመቅረብ እገዳውን ለማሠረዝ ችለዋል። ለኮትስ ይህ ገጠመኝ የትረካን ኃይል ያመለከታል።በደቡብ ካሮላይና ቻፕን ነዋሪ የሆነችው በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ነጭ መምህር ሜሪ ዉድ መጽሐፉን አንብባ በጣም ስለወደደችው፤ በክፍሏ ውስጥ አሳማኝ የሆነ ጽሑፍ እንዴት መጻፍ እንደሚቻል ለማሣየት ትጠቀምበት ነበር።መጽሐፉን በማስተማሯ ብቻም ከሥራ ልትባረር ነበር።

የመጨረሻውና ረጅሙ ምዕራፍ፥ የሚመለከተው፥ ደራሲው በመካከለኛው ምስራቅ፥ ለአስር ቀናት ያደረገውን ጉዞ ነው።እንደ ሴኔጋሉ ሁሉ ፣ በአካባቢው ያደረገው የመጀመሪያው ጉዞ ነበር። ዓይኑን የከፈተለት። «እስካሁን ከጎበኘኋቸው ቦታዎች ሁሉ፣ እንደ ፍልስጤም በቅፅበት የሚያበራ ፣ደማቅ ብርሃን የሚፈነጥቅ ሌላ ሥፍራ የለም»ይላል።ይህም የሆነበት ምክንያት በየቦታው የለመደውን የተገዥነት ምልክት ስላስተዋለ ነው።በአሜሪካ ጥቁር መሆንና በመካከለኛው ምስራቅ ፍልስጤማዊ መሆን መካከል ያለው ተመሳሳይነት እጅግ ብዙ ነው። “መንግሥቱ በድንበሯ ውስጥ ላሉ ፍልስጤማውያን የሚያስተላልፈው መልዕክት …’ሌላ ቦታ ሄዳችሁ ብትኖሩ ይሻላችኅል” የሚል ነው ሲል ኮትስ ይፅፋል።ኮትስ በጽሑፉ ይህንን ሐሳብ ቢያስተጋባም፥ የእሱ ታሪክ አለመሆኑንን ይገነዘባል። «ፍልስጤማዉያን በትክክል መታየት ካለባቸው፥ በዘራፊዎቻቸው ወይም በጓዶቻቸዉ ሳይሆን በራሳቸው እጆች በተከሸኑ ታሪኮች አማካኝነት ብቻ ነው» ይላል።

በፍልስጤማውያን ምሬት ላይ በሚያተኩረው ምዕራፍ ላይ፥ በፍልስጤማውያን ቤቶች ጣሪያ ላይ የዝናብ ውኃን ለማቆር የውኃ ማጠራቀሚያ ማየቱን ይናገራል። “በዌስት ባንክ መንደሮች፥ ተራ የወታደር ካምፕ የሚመስሉኝ የነበሩት ሰፈሮች ግን ትላልቅ የመዋኛ ገንዳዎች ያሏቸውን ክበቦች አይቻለሁ” በማለት ያነፃፅራል።

Share this post