የ32 ዓመቷ ፈረንሳዊት ባዮኬሚስት ጄሲ ኢንሾስፔ በብዙ ተወዳጅነት ያተረፉላት ሁለት መጻሕፍቶችን ጽፋ ለንባብ አብቅታለች። መልክቶቿን የምታስተላልፍበት ‘Glucose Goddess’ በሚለው የኢንስታግራም ስሟ የምትታወቀው ጄሲ ፤ 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተከታዮች አሏት። ጄሲ በደም ስር ውስጥ ያለን የስኳር መጠን (ግሉኮስ) በአንድ ቦታ የረጋና የማይለዋወጥ እንዲሆን ለማድረግ መሞከር አስፈላጊ መሆኑን አበክራ ታስረዳለች።
ከፍተኛ እውቅናን ያተረፈላት መጽሐፏ ‘The Glucose Revolution’ በሚል ርዕስ ያዘጋጀችው ሲሆን፤ ይህም ግሉኮስን በተመለከተ ውስብስብ ሳይንሳዊ እውነታዎች ዝርዝር መረጃዎች የያዘ ነው።ርዕሱ እንደሚያመለክተው፤ መጽሐፉ ትኩረት ያደረገው “አካላችን ሁሌም የሚያምረውና የሚመኘው ሞለኪውል” ግሉኮስ ላይ ነው። ሰውነታችን ግሉኮስን በተገቢው ሁኔታ እንዲያገኝ የአመጋገብ ስርአትን ማስተካከል ይገባል ትላለች። ስኳርነት ያላቸውን ምግቦች (ግሉኮስ)ን ከመጠን በላይ መውሰድ እንደ ድካም፣ የሰውነት መዛል፣ ስጋት፣ የመንፈስ ጭንቀትና የስሜት መናወጥን ስለሚያስከትል ጥንቃቄ ማድረግ ይበጃል ስትልም ትመክራለች – ጄሲ ኢንሾስፔ።
ግሉኮስ ምንድን ነው?
ግሉኮስ ስኳርነትና ስታርች ( እንደ ዳቦ፣ ሩዝ ፣ፓስታ፣ ድንች አይነት) ካላቸው ምግቦች የሚገኝ ለሰውነት ጉልበት የሚሰጥ ንጥረ ነገር ነው። ስኳር (ለምሳሌ ፤ ሙዝ፣ ብስኩት፣ ብርቱካን፣ ለስላሳ መጠጦች) ና ስታርች አይነት ምግቦች በመብላት ፤ ለሰውነታችን ግሉኮስ እናደርሰዋለን።ለሰውነታችን ከበቂ በላይ ስኳር ከላክንለት፤ የስኳር መጠኑ አለቅጥ ከፍ ይላል።የተራራ ጫፍ peaks መልክን ይያዛል።ትንሽ ቆይቶ በተቃራኒው አለቅጥ ወደታች ይወርዳል። በዚህ ጊዜ አለሰዐቱ ይርበናል። አሁንም አሁንም ጣፋጭ ነገር መብላት ያምረናል። በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን በተደጋጋሚ ከፍ እያለ ጫፍ ሲደርስ በአካላችን ላይ የሚያመጣው መዘዝ አለ።ለአብነት ያህል እብጠትና ቁስለት ሊያስከትል ይችላል። ወደታች ሲወርድ ደግሞ ድካምና ረሃብ ያስከትላል። በደማችን ውስጥ የስኳር መጠን በተደጋጋሚ ከፍ እያለ ጫፍ የሚደርስ ከሆነ፤ ቅድመ-የስኳር በሽታ (pre-diabetes)፣ ሁለተኛው አይነት የስኳር በሽታ (type 2 diabetes) ና በ polycystic ovary syndrome (PCOS) የመያዝ ዕድላችንን ከፍ እናደርጋለን።
ጄሲ ኢንሾስፔ ከምትሰነዝራቸው ምክሮች መካከል፤ ቁርሳችን ብዙ ፋይበር ያላቸውን ምግቦች መመገብ፣ጣፋጭ ምግብን በባዶ ሆድ ከመብላት ይልቅ ከአትክልት ምግብ በኋላ መብላት፣አትክልቶችን ከካርቦሃይድሬት ምግቦች በፊት መብላት መካከል የተወሰኑት ናቸው።እንደዚሁም ምግብ በልተው ከጨረሱ በኃላ በእግር መራመድ፣ ከካርቦሃይድሬት ምግቦች ከመመገብ በፊት ከፖም፣ ሲደር የተዘጋጀ ኮምጣጤ (አቼቶ) መጠጣት ጥሩ ነው ትላለች።
በጄሲ ኢንሾስፔ የኢንስታግራም ገጽ ላይ ካርቦሃይድሬት ምግቦች የሚፈጥሩትን ከፍታ ና ዝቅታ በተለያዩ መንገዶችን የሚያሳዩ በርካታ ሥዕላዊ መግለጫዎች አሉ። ሁለት ተመሳሳይ የስኳር ውጤቶች፣ አንዱ ከአትክልት በፊት ሌላኛው ደግሞ አትክልት የሌለበት፣ ስንወስድ ወደላይ የሚወጡበት ደረጃ ይለያያል።ይህም ማለት ከአትክልት በኋላ ብንወስዳቸው በጤንነታችን ላይ ያን ያህል ጉዳት አያደርሱም ማለት ነው።
ጄሲ ኢንሾስፔ እንደምትለው በደም ውስጥ ያለን የስኳር መጠን ለመቆጣጠር ፤በጤናማ ቁርስ መጀመር በተቀሩት ሰዓታት ያለውን የምግብ ፋላጎትን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ዕድል ይሰጣል።ጥዋት ላይ ሆዳችን ባዶ ስለሚሆን፤መጀመሪያ ላይ የምንቀምሰው ነገር ለውጥ ያመጣል።በዚያን ጊዜ የምንበላው ነገር ሁሉ በቀጥታ ወደ ደማችን ሠርጾ ስለሚገባ ቁርሳችንን በጣፋጭ ነገር መጀመር አይመከርም።ይልቁንም ከፍተኛ ፋይበር ያዘሉ ምግቦች ብንመገብ ይሻላል።(ለምሳሌ አትክልት፤ እንደ ቲማቲም፣ካሮት እና ሠላጣ፣ ያልተፈተገ የጥቁር ስንዴ ዳቦ ፣አጃ፣ ቡናማ ሩዝ፣ ጥራጥሬዎች: ባቄላ፣ምስር እና ሽንብራ) ይገኙበታል።
ጄሲ ኢንሾስፔ ጭማቂ ፤100% ከፍራፍሬ የተውጣጣ ቢሆንም እንኳ፤ጥዋት ላይ መጠጣቱ ጥሩ አይደለም ትላለች።ፍራፍሬ ተጨምቆ ወደ ጭማቂ ሲቀየር የፋይበር ይዘቱን ያጣል፤ ስኳር ብቻ ይሆናል ።ጭማቂ ከመጠጣት ይልቅ ፍራፍሬውን እንዳለ መብላቱ ይሻላል ትላለች።
Life-Changing Glucose Hacks: easy tricks that will change how you feel forever | Episode 3 of 18