አስፋው ዳምጤ የመንግስቱ ለማ ስራዎችን በተመለከተ

አስፋው ዳምጤ የመንግስቱ ለማ ስራዎችን በተመለከተ

በአንጋፋው ደራሲ ሃያሲና የኢኮኖሚ ባለሙያ አስፋው ዳምጤ የተሰናዳው “የአማርኛ ጥበበ ቃላት ቅኝት” የተሰኘ መፅሐፍ፣ ሐምሌ 2015 ላይ በሁሴን ከድር አሰናኝነት ታትሟል ፡፡ መፅሐፉ፤ የመቶ ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ የስነ ጽሁፍ ታሪክን የሚተነትን  ሲሆን የሚከተለው ከመጽሐፉ የተወሰደ ነው ፡፡

“በ1950ዎች አዳዲስ ደራስያን መነሳታቸውንና መግነናቸውን በቀደሙት ገጾች ጠቁመናል።በዚያ ወቅት ዕውቅናን ካተረፉት መካከል እነ አቤ ጉበኛ፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ መንግስቱ ለማ እና ጸጋዬ ገብረ መድህን በ1960ዎቹም ቀጥለው እናገኛለን።

ከመካከላቸውም ጸጋዬ ገብረ መድህን በ1959 የመጨረሻ የዓመት የቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅትን የሥነ ጽሑፍ ሽልማት አግኝቶ የነበረ ሲሆን፣ መንግስቱ ለማም በለጠቀው ዐሠርት መባቻ ላይ በ1960 የዚሁ የቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ ሽልማት ተሸላሚ ሆነ።

መንግስቱ ለማ በዕድሜ ከሁሉም አንጋፋ መሆን ብቻ ወደ ድርስቱ ዓለምም የገባው ገና በተማሪነቱ ነበር። ከአረፈ በኃላ በዕውቁ የብዕር ሰው በመስፍን ዓለማየሁ አርታኢነት ፣ በ1988 በታተመው የመንግስቱ ለማ ግለ ታሪኩ (የሕይወት ታሪኩ የጅማሮው ቁንጽል ክፍል) መጽሐፍ ውስጥ ስለ ሕፃንነቱ እና የወጣትነቱ ዘመን ጠቃሚ መረጃዎች ከራሱ ብዕር እናገኛለን።እዚያ ውስጥ ወደ ድርሰት ዓለም አገባቡ ሁኔታ እንዴት እንደነበር እናስታውሳለን። ከ 130-34 በሚገኙት ገጾች ላይ በ1950 ባሳታመው በየግጥም ጉባኤ ውስጥ ከወጡት መካከል በጠራ ጨረቃ የሚለው ግጥም እንዴትና ለምን እንደተፃፈ የሚያትተው ለዚህ በዋቢነት ሊጠቀሱ ከሚችሉት አንዱ ነው።

ይሁንና መንግስቱ የ 1960ዎቹ ዐሠርት የጀመረው ጠልፎ በኪሴ የሚለውን ተውኔቱን በ1961 በማሳተም ሲሆን፣ ይፋዊ አስተዋፅኦውን የደመደመው ደግሞ ባሻ አሸብር ባሜሪካ የተሰኘውን የግጥሞች ስብስብ በ1967 በማሳተም ነበር።በነዚህ መካከል ስለቲያትር አፃፃፍ ብልሃት አንዲት የኢልቦለድ ድርሰትም አቅርቧል።

ጠልፎ በኪሴ፤ ላይ ላዬን እያዋዛ በጋብቻ፣ በተለይ ይዅም የዛሬዋ ልጃገረድ ዕድሜ እንደ ጥንቲቱ ጨቅላ ትንሽ ባለመሆኑ፤ ይህ ዕውነት አዲስ ሁኔታዎችን የሚያስከትል መሆኑን (በፈገግታ) ጣል የሚያደርገው ነው።

ባሻ አሸብር ባሜሪካ ውስጥ የተካተቱት ግጥሞች በተፆፉበት ዘመን (1950ዎቹ) በሳንሱር ምክንያት ለመታተም የማይችሉ ዓይነቶች ስለነበሩ፣ “የፖለቲካ እስረኛ የነበሩ ግጥሞች” ሲል ገልጹዋቸዋል።ከእነዚህ መካከል በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው ለስብስቡ አጠቃላይ ርዕሱን ያቀበለው ባሻ አሸብር ባሜሪካ ነው።ከቀሩት ውስጥ ሁለቱ ወቅቶቻቸውን ጠቋሚ ናቸው ተብለው የነበረ ቢሆንም እንደማንኛውም ሁለንታዊነት እንዳለው የጥበብ ሥራ ሁሉ ተመሳሳይነት ያላቸው ሁኔታዎች እና ወቅቶች የሚገልጹ ናቸው ማለት ይቻላል።

ለምሳሌ፦ ሹመት የሚለውን ግጥም እንውሰድ

“ውስጠቀ ግጥሞች” የሚል እንደ “ውስጠዘ” መሰል መለዩ ገጣሚው ሰጥቷቸዋል።

እነሆ ግጥሙ፦

ወይ ካልቸበቸቡ
ወይም ካልሰረቱ
ወይ ካላሳባቱ
ማ ለማ ያቀምሳል ከዚያ ከሱረቱ?

ሌላው ፣ ሐሳብን በሐቅ ስለ መግለጥ፣ በመላው ዓለም ዝናና ታዋቂ ከነበረው ቻይናዊ የብዕር ሰው ፣ሉ ሕሱን (ቹ ሱጄን) ሥራዎች መካከል ፣ መንግስቱ ተርጉሞ ያቀረበው ግጥም ነው። ይህም የቀደመውን ዘመን (የአፄውን) የሚመለከት ይምሰል እንጂ ይበልጥ የለጠቀውን የሚመለከት አድርገው የተረዱት አንባብያን ጥቂት አልነበሩም።ሆኖም ግን ሁለንታዊነት ያለው ነውና ባንድ ቦታና ጊዜ ልንወስነው አይገባም።ግጥሙ ሐሰት መናገር የሚያዋጣ እውነት መናገር ጣጣ የሚያመጣ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ የሚገኝና፣ የመጀመሪያውን የሚጸየፍ ሁለተኛውን የሚወድ ሆኖ፣ ግን ጣጣውን የሚፈራን ሰው እንቆቅልሽ ምንም ባለማለት የሚፈታ ነው። የእውነቱን ተናግሮ የመሸበት ያድራል ተቃራኒ መፍትሔ።እነሆ መደምደሚያው
ጠባይህ ከሆነ እንደዚህ እንዳልከው
“ሃ ሃ ሃ አያችሁት ያንን ልጅ” ማለት ነው
ማለት ነው “በዝጌሃር! ሆሆ! ሂሂ! ሃሃ!
ሆሆሆ! ሆሆሆ!
ሄሄሄ! ሄሄሄ!”


አስፋው ዳምጤ ‘የአማርኛ ጥበበ ቃላት ቅኝት

አሰናኝ፦ ሁሴን ከድር ሐምሌ 2015

Share this post