“ሬሳ ሲመጣ መንገድ ላይ እንዳትቆም” እያለች ዱሮ እናቴ ትከለክለኝ ስለነበር ለቀስተኞች ሲመጡ ባየሁ ቁጥር መንገድ ለቅቄ እሸሽ ነበር።በሰፈራችንም ሰው የሞተ እንደሆን ልጆች በዚያ አካባቢ ዝር እንዳንል እንከለከል ስለነበር የልቅሶ ትዕይንት ምን እንደሆን ብዙ ሳላውቅ አደግሁ።
በቅርቡ ከአዲስ አበባ ውጪ ስሄድ ከመንገድ ላይ ያጋጠመኝ ሁኔታ ግን ያደግሁበት አካባቢ የነሳኝን ትልቅ ነገር አስተማረኝ።ለካስ በመንገዳችን ላይ በምትገኝ አንዲት መንደር አንድ ትልቅ ሰው ሞተው ኖሮ የተሳፈርንበት መኪና በብዛት የያዘው ለቀብራቸው የሄደ ለቀስተኛ ነበር።እለቅሶው ቦታ ስንደርስ ሰው ሁሉ ወረደ።አራት ሰው ብቻ ይዞ መኪናው አይሄድም ስለተባልን የቀረንውም ሳንወድ የልቅሶው ዕድምተኞች ሆንን።ልቅሶም ለካ ውበት አለው! “ሳንወድ አለቀስን” እያሉ የሚናገሩትም ለካ ውነታቸውን ነው።ማልቀስ መቻል የኢትዮጲያውያኖች ችሎታ ቢሆንም አልቅሶ ማስለቀስ ግን ካንጀት ላለቀሰ ሰው የተሰጠ ነው። አቤት ድምፃዊ፥ አቤት ገጣሚ፥ የተኛን አንጀት ያላውሳል፤ የደረቀውንም ዓይን ይፈነቅላል።ዕድምተኞውን ሁሉ አልቃሽ ያደርገዋል።እኔን የነካኝና ልናገረውም የምፈልገውም ስለዚህ ሳይሆን ባሕል ስለፈጠረው የልቅሶው ሥርዓት ነው።
ከመኪናው ውስጥ ስወርድ ለመጀመርያ ጊዜ ሃሳቤን የወሰደችው በመንገዱ ዳር ዳር፥ ላይ ታች እያለች የምታለቅሰው ሴት ወይዘሮ ነች። ቀሚስዋን ከፊት ለፊት እስከመቀነት መታጠቂያዋ ተርትራ ደረቷን ጥላለች።ከአንጀቷ ለማልቀሷ ምልክት ከዓይኗ የሚወርደውን እንባ ፊቷን አልብሶት ደረቷን አርሶታል።በእርግጥ ይቺ ሴትዮ የእምባ ጥገት ነች። በጣም ያልወደድኩት ነገር ቢኖር ደረት ምቱን ነው።አንዴ ከጀመረች በትግል በገላጋይ ነው የምታበቃው።ከአፏ የሚወጣው ቃል ልብን ይነካል።እኔም ልቤ ተነካና ሁለት ዘለላ ዕምባ ያህል ወረደኝ።ብዙ ለማልቀስ ስላልፈልግሁ ከአጠገቧ ዞር አልኩ።የሟቹ ቤት በግምት እኛ ከቆምንበት ፫፻ ሜትር ላይ ስለነበር የዚሁ ሁሉ ጉዞ ወደዚያ ነው።ሰዎቹ መጥተው ሲገናኙ ልዩ ሥርዖት አለው።ከየክፍሉ ለሟቹ የቅርብ ዘመድ የሆነው ሰው ከሌላው ክፍል መሪ አልቃሽ ጋር ይተቃቀፋሉ።ደረት ለደረት ተለጣጥፈው የሚነጋገሩት ልዩ ነገር አለ።እነሱ ይህን ሲያደርጉ አጃቢዎቻቸው ጩኸታቸውን አቅልጠው በዙርያቸው ይሆናሉ።ጐንበስ ቀና እየተባለ አንዱ የሟቹን ለጋስነት፥ ጀግንነትና የነሱን መጐዳት ከገለጸ በኋላ ይረገዳል።እዚህ ያለው ሥርዓት በዚህ ተፈፅሞ መንገድ ይጀመራል።ይህ እንግዲህ እለቅሶው ቦታ ከመድረሳቸው በፊት ሲገናኙ የሚደረገው ሥርዓት ነው።ከየአቅጣጫው የሚመጣው ሕዝብ በዚህ ዓይነት ከተዋሃደ በኋላ በአራት ትልልቅ ክፍል ብቻ እለቅሶው ቦታ ይደርሳል።
እዚያ ሲደርስ ጩኸት ይበዛል። ሬሳው ወደተቀመጠበት ቦታ ተሄዶ እጅ ከተነሳ በኋላ ሴቶቹ ወደ ሴቶቹ፥ ወንዶቹ ወደ ወንዶ ይሄዳሉ። በሴቶቹ አደባባይ ሁለት ክፍል አለ።ያገቡና ያላገቡት።ያላገቡት ሥርዓታቸው የልጅነት ጠባይ ያለበት ይመስላል።የሚይዙት የሟቹን የላይ ልብስ ማለትም ነጠላ፥ ኮት፥ ካፖርት እና ሸሚዝ ነው።ይሄ ሁሉ ተጠቅልሎ መልክ ባላቸው ሁኔታ አንድ ይሆናል። ከዚያ እንግዲህ ይህንን እየተነጣጠቁ ያለቅሳሉ።የሚናጠቁት መሪ ለመሆን ሲፈልጉ ነው። አሸንፋ የወሰደችው መሪ የመሆን ዕድል አላት።ከአሸንፈች፥ ማለትም ሙሉ ለሙሉ ከያዘች ትተዋለች።ይህን የተቀሩት ዙሪያ ይቆሙና እሷ ዳር ዳሩን ትዞራለች። አንዳንዴም እንደሸኖቴ ትሰብቀዋለች።ሁለት ሦስቴ ከዞረች በኋላ ወደ መሐል ትገባለች።በዚህ ጊዜ እንደገና መናጠቅ ይጀምራሉ።አንዳንዴም ይባረራሉ።እንባቸው ግን ልክ የለውም።
ያገቡት ግን ሥርዓታቸው ለየት ያለ ነው። በጣም የቅርብ ዘመድ የሆነችው መሐል ሆና ትመራለች። የሟቹ ሱሪ ባገቡት ሴቶች ዘንድ እንደ ፎቶግራፍ ነው። እሱን እያገላበጡ ያዩና አንዴ ባንድ ዓይነት ዜማ ሲያለቅሱ ልብ ይበላሉ።በመጨረሻም አንዷ ከመሐከል ግጥም ስትገጥም እየተከተሉ ይቀበሏታል።እኔም ልቤን ባር ባር አለኝና በእንባ ተነከርኩ። ከአንጀቴ አለቀስኩ። ያላወቅሁት ከእጁ ያልበላሁት ሰው አንሰቅስቆ አስለቀሰኝ።የዜማ ወዳድነቴ ይሆን?
እንደ ሥርዓቱ ወንዶቹና ሴቶቹ ከሆነ አይደባለቁም።የተወሰነ ቦታ አለ። ያንን ማለፍ ነውር ነው።እኔ ግን መቼም ለወሬ ሙት ነኝና ዝም ብዩ ተደባለቅሁ።ምናልባት በኀዘን ራሱን ስቶ ይሉኝ ይሆን? እንጃ።በመጨረሻ ሳይ ወንድ ስለሌለ የወንዶቹን ሥርዓት ለማየት ደግሞ ጥሼ የመጣሁትን የሥርዓት ግድግዳ እንደገና ተራምጄው ወደ ወንዶቹ ሄድኩ።
ወንዶቹ ደግሞ የኳስ መጫወቻ የሚያህል ቦታ ከበው በመካከሉ የሚታየውን የፈረስ ትዕይንት ያማሙቃሉ። እዚህ ጉግስ፥ ዝላይ፥ ፉከራ፥ ሽለላ ነው እንጂ ለቅሶ የለም።እዚህ ወኔ ይቀሰቀሳል እንጂ እምባ አይመጣም።ፈረሱ በርከት ካለ፥ ማለትም አርባ አምሳ ከደረሰ ሟቹ ጀግና እንደነበር ይታወቃል።ቀረርቶውና ፉከራውን ስሰማ የት አየኸው አትበሉኝና አድዋ ትዝ አለኝ።በጦሩ ይሰበቃል፤ ግን አይወጋበትም።በጋሻው ይመከታል፤ የተወረወረ ግን የለም።ስድስት ፈረሰኛ ካንድ ወገን በተርታ ተስልፎ ሲሄድ ከፊት ለፊት ደግሞ ስድስት ፈረሰኛ ይመጣል። አንድ አይነት ዜማ እየተዜመ መጥተው ሲጋጠሙ ይዘበራረቁና ፉከራው ያስተጋባል።የሟቹ ጀግንነት የገደለበት፥ የማረከበት፥ ያደነበት ጫካ እንኳን ሳይቀር ይተነተናል።ቀረርቶው ልቤን ሲበላኝ፥ ፉከራው ወንድነቴን ቀሰቀሰው።ጀግና ከሞተ በኃላ እንኳን ወንድን ወንድ ያደርጋል።
ሁለት ሰዓት ተኩል ያህል ያየሁት የልቅሶ መስተንግዶ ትልቅ ትምህርት ሰጥቶኛል።አልቃሻ ማለት ስድብ ነው።አልቃሻ ማለት ግን ሞያ መሆኑን ተገነዘብኩ።ለቅሶም ለካ መረሳት የማይገባው ቅርሳችን ነው!
መንግሥቱ ፡ ለማ ። የለቅሶ ፡ መስተንግዶ ። [ ከመነን ፡ መጽሔት ] ። አዲስ ፡ አበባ ፡ ሰኔ ፡ ፲፱፻፷፮ ፡ ዓ ፡ ም ።
፪ኛ ፡ ዓመት ፥ ቍ ፬