ባዶ ወንበር- ዮሐንስ አድማሱ

ባዶ ወንበር- ዮሐንስ አድማሱ

ዕውቁና ተወዳጁ ባለቅኔ ዮሐንስ አድማሱ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ታላቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ ገጣሚ እና ሃያሲ የነበረ ሲሆን በ1960ዎቹ በተደረገው የተማሪዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ወቅት ግምባር ቀደም በመሆን ከታገሉት አንዱ ነው።በደብረሊባኖስ መስከረም 29 ቀን 1929 ዓ.ም የተወለደው ዮሐንስ በአፍላ እድሜው በ1952 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ገብቶ በትምህርት ጉብዝናው እና በፖለቲካዊ ተሳትፎው ምክንያት የበርካቶችን ትኩረት ለማግኘት ችሎ ነበር። በ1955 የሶስተኛ ዓመት ተማሪ እያለ “እስኪ ተጠየቁ” የሚለውን ረጅም ግጥሙን አቅርቦ የቀዳማዊ ኀይለሥላሴን ሥርዓት በመውቀሱ ከዩኒቨርስቲ ለመባረር በቅቷል። በ38 ዓመቱ በሰኔ 1967 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ዮሐንስ ከፃፋቸው ግጥሞች መካካል- “ባዶ ወንበር” የሚል ይገኝበታል። ግጥሙ ለመጀመርያ ጊዜ የታተመው ውይይት-በኢትዮጵውያን የዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበር የሚታተም መጽሔት ሐምሌ 1962 ላይ ነው።

ለኔ አልተፈጠርሽም።
መሄድሽን ሳውቀው ሁኖ እንደተማላ፤
ያ መናጢ ጊዜ ሸሩን እያሰላ፤
ሁሌ መጥበቅ እንጂ ከቶ የማይላላ፤
ውሻሉን ሰዶታል የግዜር የግራ እጁ፤
አብሮ አደግ ወዳጁ።

አሁን ሁሉም አልፎ ሆነና ትዝታ፤
ልቤ በጸጥታ፦
ልቤ በዝምታ፦
ጭው ጭር ጫ ብሎ አይቶ አጣ በረሃ፤
ለብዙ ዘመናት የናፈቀው ውኃ፤
እዚያ ደንጊያ
እዚህ ደንጊያ ቋጥኝ ብቻ አግጦ
የገረጣ አሽዋ መልቶ ተለጥልጦ፤
የቀጨጨ ቊልቋል፤ ግንትርትሩ ግራር፤ ሁሉም አቀጭሞ፤
ድርቅ የገነነበት ሰለባ ፈጽሞ፤
እንዲህ ሁኗል ልቤ።

ያሁኑ በረሃ ለም የነበር ቀድሞ፤
እቤቴ ውስጥ ሁኜ፤
ባራቱ ግድግዳ በወለል በጣሪያ ድንገት ተወስኜ፤
መለስ ቀለስ ብዬ ግራ ቀኝ ብዞር፤
ጐኔን ዳበስ፤
ዐይኔን አበስ፤
ብሞክር ባደርገው ብሠራ ብፈጥር፤
ወምበር ጠረጴዛ፤
እንደተቈጡት ልጅ የሆነ ቀዛዛ፤
ሁሉም ሁለመናው ያያኛል አፍጦ፤
በሚጮህ፤በሚንር በብራቅ ጸጥታ፤

ጸጥታው አቀፈኝ፤
አቀፈና አነቀኝ
አክትሞ ሠልሶ ጣለኝ ለዝምታ።
ከጣለኝም ኋላ እየቀሰቀሰ
ይቛጥራት ገባ ነፍሴን በራፊ ጨርቅ እየበጣጠሰ።

የተቀመጥሽበት ወንበር ባዶ ሁኖ፤
ዐይኔ እየነገረኝ፤ግና ልቤ ልቡ በትዝታ ባክኖ፤
አሻፈረኝ አለ ለመቀበል አምኖ።
ዐይኔ የሚያየውን ባዶውን ወንበር፤

“አለች አለች፤
ተቀምጣበታለች፤
አለች አልሄደችም” ይላል ልቡ ልቤ።
የዋሁ ሰበቤ።
ያውና ዐይኗ
የማየቷ ጸጋ
ያውና እጅዋ
ዘንጠፍ ዘርጋ ብሎ
ያውና ከንፈሯ
ፈገግ ፈገግ ሲል፤ ጥርሷ እየፈለቀ በልዩ ፈገግታ፦
እንደ ማልዳ ብርሃን ሌሊቱን የሸኘ፤

በወፎች ዝማሬ ታጅቦ ሲመጣ ውበት እየናኘ።
ባዶ አይደል ወንበሩ፤
ከዳር ከድንበሩ፤
ትፈልቅበታለች ተቀምጣ ደርብባ፤
የዋህ ንጹሕ ደንሴ የውበት አበባ።”
ይላል ልቡ ልቤ፤
የዋሁ ሰበቤ።

ለኔ አልተፈጠርሽም ሲጀምር ከጥንቱ፤
የውልታ ሆነ ፍቅራችን መልክቱ
ባዶ ወንበር።

Share this post