ካናዳዊቷ ማርጋሬት አትውድ በ1985 ያሳተመችው ልብ ወለድ መፅሐፍ ከገሀዱ ዓለም ፓለቲካ የተቀዳ ቢሆንም ከመቼውም ጊዜ ይልቅ የዛሬውን ዘመንን የሚተነብይ መፅሐፍ ነው።
ባለሰፊ ክዳን ኮፊያና ቀይ ካባ በአእምሮችን የሚከሰትልን አንድ ነገር የሴቶች ጭቆና ነው። ይህንን ምስል በነፍሳችን እንዲታተም ያደረገው ማርጋሬት አትውድ እንደ አውሮፖውያኑ የዘመን ቀመር በ1985 ያሳተመችው The Handmaid’s Tale (የደንገጡርዋ ወግ ) የሚለው ልብወለድ ሲሆን ሴቶች ለማህረሰቡ ልሂቃን አባወራዎች፤ ልጆች እንዲወልዱላቸው ባርነት ያደሩበትን ሁኔታና ይህንን ለማመልከት ይህ የደንብ ልብስ የሚለብሱበት በቅርብ ዘመን የሚጠበቅ ተውኔታዊ ዓለም (near-future dystopia) ስዕልን ያቀርብልናል። ከሰላሳ ዓመታት በላይ ይህ ምስል በዓለም ዙርያ በመፅሐፍ ልባስ ላይ፣ ፊልም ላይ ፖስተሮች ላይ፣ በቲቪ ተከታታይ ድራማ ማስታወቂዎች በጉልህ ሲታይ የቆየ ሲሆን ለሥነ-ተዋልዶ የሚደረጉ መብቶች ትዕይንት ሕዝቦች ና ሰልፎች ላይም ሴቶች ለብሰው መታየታቸው የተለመደ ነው፡፡
ከነዚህ ምስሎች በሚበዙበት ላይ የምናያት ደንገጡር ምንም እንኳን እርግጠኞች ባንሆንም የወጉ ተራኪ የሆነችው ኦፍሬድ (Offred) ናት፡፡፡ በጊልያድ ሪፐብሊክ ደንገጡር የሆነችው ኦፍሬድ ከአለቃዋ ፍሬድ ጋር ዘወትር ወሲብ የመፈፀም ግዴታ ተጥሎባታል፡፡ የስምዋ ትርጉም የፍሬድ (“of Fred”) ይህን ያመለክታል፡፡
በርካታ የገዢው መደብ አባላት ሴቶች በአካባቢያዊ በካይ መርዞች እንዳይወልዱ ሆነው ከመከኑ በኃላ ለዚሁ ልጅ የመውለድ ሚና በመንግሥት ቁጥጥር ከዋሉ ስር ወላድ ሴቶች አንዷ ናት፡፡ የአሜሪካ መንግሥት በመፈንቅለ ምንግሥት ተወግዶ ጊልያድ የተሰኘ ዙፋነ እግዜአብሔር (ሃይማኖታዊ) መንግሥት ከመቇቇሙ በፊት ሉቃስ ከተባለ ሰው ጋር ተጋብታ አንዲት ሴት ልጅ ወልዳለች፡፡
አትውድ ልብወለዱን የጻፈችው የመጻኢውን ጊዜ የማውጠንጠኛ ታሪክ አድርጋ ነው፡፡ ይህም የቴክኖሎጂ ዕድገት ከዛሬው ዘመን እምብዛም ለውጥ ሳያሳይ ሊከሰት የሚችል ሁነትን በምናብ የሚስል ትረካ ነው፡፡ በሌላ አባባል የሳይንሳዊ ልብወለድ ጭራቆችን ፣መንኩራኩሮችን ገፀ ባህሪያት ሲያደርግ አውጠንጣኝ ልብወለድ ደግሞ በእውን ሊከሰት የሚችልን ኩነት ይስላል፡፡ እያንዳንዱ የመጽሐፉ ገጽታ መጽሐፉ በተጻፈበት በ1980ዎቹ በተከሰቱ ማኅበራዊና ፖለቲላዊ ኩነቶች የተጠነሰሰ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት የአትውድ ልብወለድ በመጀመሪያ ከታተመበት ጊዜ አንስቶ በተደጋጋሚ በታተመባቸው ጊዜያት ሁሉ እንግዳ በሆነ ሁኔታ የወቅቱን ሁኔታ የሚያንፀባርቅ ሆኖ ይገኛል፡፡ የመጀመሪያው ህትመት በ1985 ሲወጣ አትውድ የታሪኩን ትልም በእውነተኛ ሁነቶች ላይ የተመሠረተ መሆኑን ለማሳየት በቃለ-መጠይቅ ጊዜያት የጋዜጣ ጽሑፎችን ይዛ ትቀርብ ነበር፡፡ መጽሐፉ ዩናይትድስቴትስ ወግ አጥባቂነት ማቀንቀን የጀመረችበትን ሁኔታ ይህም በሮናልድ ሬገን ለፕሬዝዳንት መመረጥን የቀኝ ክንፍ ክርስቲያናዊ ቡድን እያጎለበተ የመጣውን ብርታትና የሥነምግባር ብዙሃን (The Moral Majority) ትኩረት ለቤተሰብና ክርስቲያናዊ አጋርነት (Focus on the Family and the Christian Coalition) የተሰኙ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ተፅዕኖ እንዲሁም የቴሌቪዝን ወንገላዊያን አገልግሎት ጅማሬ ያሳያል፡፡ በመጽሐፉ ላይ ሴሬና ጆይ የተባለችው ገፀባህሪያት በአንድ ወቅት የሃይማኖታዊ መንግሥት አስፈላጊነት ስታቀነቅን የነበረች የቴሌቪዥን ወንጌላዊት ስትሆን አሁን ግን በሴቶች ላይ በተጣለው ግዳጅ ሳቢያ ኑሮዋ በቤት ተወስኗል፡፡ አትውድ ስለሰሬና ጆይ እንዲህ ስትል ትጽፋለች፡፡ “አሁን ንግግር አታቀርብም፤ አንደበቷ ተሸብቧል፡፡ ውሎዋ ቤት ሆኗል፤ ሆኖም ይህ የተስማማት አትመስልም፡፡ አሁን የተሟገተችለት ርዕዮተ ዓለም በእውን ተፈፅሞ ማየቱ ምንኛ ብስጩ አድርጓት ይሆን፡፡”
አትውድ ካናዳዊት ብትሆንምና ራቅ ስላለ ጊዜ ብትጽፍም -ጆይስ ካሮል ኦትስ በኒውዮርክ ታይምስ የመጽሐፍ ቅኝት (The New York Review of Books) የመጽሐፉ መቼት 2005 ሊሆን እንደምችል ጠቁማለች- የመጽሐፉ ርዕስ ጉዳይ በ1980ዎቹ የነበረችው ዩናይትድ ስቴትስ እንደሆነችና ትኩረቶቹም ክርስቲያናዊ አክራሪነት፣ ሥነ ምህዳራ ጉዳዮችና የሴቶች የተዋልዶ ጤና መብቶች እንደሆነ ጠቁማለች። በወቅቱ በአሜሪካ ውርጃን በመቃወም ይካሄድ የነበሩ ዘመቻዎች “የአርምሞ ጩኸት” (‘The Silent Scream) የተሰኘ የፕሮፓጋንዳ ቪዲዮ የውርጃ ክሊኒኮች በቦንብ ማውደምና ማቃጠል እንደዚሁም የሰብዓዊ መብት ዋስትና ላልተወለዱ ፅንሶች እንዲሰጣቸው የሚጠይቅ ሕግ መረቀቅ ይጠቀሳሉ፡፡
የሬጋን አስተዳደር ለረዥም ጊዜ የቆየ ፖሊሲን በመለወጥ የአሜሪካ መንግስት ድጋፍ የሚያቀርበው ‘ተፈጥሮአዊ‘ የቤተሰብ ዕቅድን ማለትም ተአቅቦን (abstinence) ለሚያቀነቅኑ ባላደጉ ሀገራት ለሚንቀሳቀሱ ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶች ብቻ እንደሆነ አዋጀ። ኤስሲ ኒውነማን የተሰኙ እንግሊዛዊ ፕሮፊሰር፥ በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ የጥናት መጽሔት ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ እንደዚህ ይላሉ “ኦፍሬድ በአጭሩ የ1970ዎቹ አንስታዊነት ወጤት ስትሆን በ1980ዎቹ ተፅዕኖው እያየለ የመጣው በሴቶች መብቶች ላይ የተነጣጠረው ዘመቻ በልብወለዳዊ ትረካ የቀረበች ሴት ናት፡፡”
በዚያን ወቅት በየአሜሪካ አስተዳደር ከነበሩ ሰዎች መካካል የደቡብ አፍሪካውን አፓርታይድ ለመቃወም የማይደፈሩ ነበሩ፡፡ ቀጣይ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡትን ዲክ ቼኒ የኔልሰን ማንዴላን ከወኅኒ መፈታት ይቃወሙ የነበሩ ሲሆን ሴናተር ጆን ማክኬይን የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ማዕቀብ እንዳይጣልበት ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ አትውድ የአፓርታይድ ዘመን ባንቱስታዎኖችን በማስታወስ በደንገጡርዋ ወግ (The Handmaid’s Tale) አፍሪካ-አሜሪካውያን በመካከለኛው ምዕራብ (ሚድዌስት) በብሔራዊ መኖሪያ “National Homelands” እንዲሠፍሩ መደረጋቸውን ትገልጻለች፡፡
መጽሐፉ ከጥቂት አመታት በፊት ወደ ፊልምነት ተቀይሮ በቴሌቪዥን በተከታታይ ሲታይ ነበር ዝነኛ ለመሆን የበቃው፡፡ የፊልሙ አዘጋጆች ፊልሙን ዘመናዊ ዳራ ለማልበስ፥ መፅሐፉ ላይ ከሠፈረው ውጭ ፥ ብዙ ነገሮችን ጨምረዋል፡፡ እንደ ኡበር የተሰኘው የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ ፣ ቲንደር የተሰኘው የስልክ አፕሊኬሽን፣ ወደ ኦፍሬድ የቅድመ ባርነት ህይወት በምልሰት በማስገባት፡፡
ግን ፊልሙ እና መፅሐፉ ይበልጥ ድል ተወዳጅነትን ያተረፈው፤ የዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነዉ መመረጥን ተከትሎ በአሜሪካ ከፍተኛ የፖለቲካ ለውጥ በመከሰቱ ምክንያት ነው፡፡ በድንገት፣ የመጽሐፉ እና የፊልሞቹ ዋና ዋና ነጥቦች ከመቼውም ጊዜ እውን የሚሆኑበት ጊዜ የተቃረበ መሰለ። በእስልምና አክራሪዎች ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ ወታደራዊ ህግን የሚያወጅ መንግስት ፣ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን ስልታዊ በሆነ መንገድ የሚያስወግድ አገዛዝ ፣ የሴቶች ተግባር መውለድ ብቻ ብሎ የሚያምን ህብረተሰብ፡፡
መጽሐፉ ከታተመበት ጊዜ ጀምሮ በደንገጡርዋ ወግ መጽሐፉ ውስጥ በጣም የሚጠቀሰው አባባል፤ በክፍሏ ውስጥ ቁም ሣጥን ላይ፤ ምናልባትም በፍሬድ ቀደምት ደንገጡር ላቲን በሚመስል ሁኔታ የተፃፈው- Nolite te bastardes carborundorum (ዲቃላዎቹ እንዲፈነጩብህ አትፍቀድላቸው።) የሚል ነው። አባባሉ ለሴቶች መብት ተሟጋቾች፤ ቀስቃሽ ሆኖ በመገኘቱ ፤ በዚህ ዘመን ብዙ ሴቶች በአካላቸው ላይ ተነቅሰውታል፡፡ ገሚሶች በሃሎዊን በዐል ላይ እንደ ደንገጡር እንዲሁም ሌሎች ተቃውሞ ሰልፎችም ይለብሱታል – እነዚህ ሁለት የልብሱ አጠቃቀሞች ለሁለት የተለያዩ መንታ አላማዎች መዋሉን ያንፀባርቃሉ በማለት ማርጋሬት አትውድ ጋርዲያን ጋዜጣ ላይ ጽፋለች፡፡ “ጨዋታ ነው ወይስ አስከፊ የፖለቲካ ትንቢት? ሁለቱንም ሊሆኑ ይችላሉን? መጽሐፉን በምጽፍበት ጊዜ ይህ ይሆናል ብየ አላሰብኩም ነበር ፡፡”