ልጆቻችንን ምን እየመገብን ነው?

በፉብሪካ ሂደት ያለፉ እና ይዘታቸው ከመጠን በላይ የተቀየሩ ምግቦች (ultra-processed foods)በልጆች ላይ ከልክ ያለፈ የሰውነት ውፍረት እያስከተሉ ነውን? ሱስ የማስያዝ ችሎታስ አላቸውን? ዶ/ር ክሪስ ቫን ቱልከን በገዛ ራሳቸው ላይ ሙከራ በማድረግ ያዪት ውጤት ሳይንቲስቶችን እንኳን ያስደነገጠ ሆኗል፡፡

በመላው ዓለም ፣ ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ የህጻናት ከመጠን በላይ መወፈር በአስር እጥፍ ጨምሯል፡፡ ለአብነት ያህል፥ በእንግሊዝ ሀገር ውስጥ 21 ከመቶ የሚሆኑት ልጆች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ  ከልክ ያለፈ ውፍረት ችግር ይከሰትባቸዋል።- ይህ እስካሁን ድረስ ከተመዘገበው ከፍተኛው ነው ፡፡

ባለፉት አስርተ ዓመታት ችግሩ ቢታወቅም እና ለመፍታት ጥረት ቢደረግም፤ይህንን ችግር ለመቋቋም የተሳነን ለምንድነው?

በቅርቡ የተላለፈው የቢቢሲ ፕሮግራም እንደሚያስረዳው፤ ባለፉት 40 ዓመታት በምዕራቡ ዓለም ሰዎች ከየሱፐር ማርኬቱ የሚሸምቷቸው የተፈበረኩ ምግቦች ፣ ሰውነታቸው ለሚያስፈልገው ካሎሪ ምንጭ ሆኗል- ለህጸናት 64 በመቶ ፣ እና ለወጣቶች ደግሞ 67 ፐርሰንት ፡፡ ዋጋቸው አነስ ያለ በመሆኑ እና በተለያዩ ሱፐርማርኬቶች በቀላሉ ማግኘት የሚቻል በመሆኑ ተመራጭ ቢያደርጋቸውም በሚያስደንግጥ ሁኔታ ሳይንቲስቶች በልጆች አካላት ላይ የሚያደርሱትን ተፅዕኖ እምብዛም አያውቁም፡፡

በርካታ የህዝብ ጤና ባለሙያዎች እና ኤክስፐርቶች አብዝተን እንደምንመገብ ይናገራሉ፡፡ ይህም አሳሳቢ ነው-ምክንያቱም ሰዎች በከፍተኛ መጠን ሲመገቡ ከመጠን ያለፈ ውፍረት እንዲኖራቸው እና ችግር ላይ እንዲወድቁ ምክንያት ይሆናል፡፡ጉዳዩ ካሳሰባቸው አገራት መካከል ፈረንሳይ እና ካናዳ ዜጎቻቸው ከመጠን በላይ የተቀየሩ ምግቦች (ultra-processed foods) ፍጆታቸውን እንዲቀንሱ በመምከር ላይ ናቸው።

ከመጠን በላይ የተቀየሩ ምግቦች (ultra-processed foods) በምዕራቡ ዓለም የምግብ ገበያ ሰርፀው የገቡ ሲሆን የሚያደርሱትን ተፅዕኖ በግልፅ መረዳት ከባድ ነው ፡፡ግን በቅርብ አመታት ከተዋወቀባቸው አዳዲስ ቦታዎች ምን መማር እንችላለን? ዶ/ር ክሪስ ወደ አማዞን ተፋሰስ በመሄድ እንዳስተዋሉት ፥ በብራዚል ገጠራማ አካባቢ ከመጠን በላይ የተቀየሩ ምግቦች (ultra-processed foods) ፍጆታ በእጥፍ ሲያድግ ከመጠን ያለፈ ውፍረት በሦስት እጥፍ መጨመሩን ነው።የዚህ አይነት ምግቦች በዚህ ራቅ ባለ አካባቢ መምጣት በአጋጣሚ የተከሰተ ነገር አይደለም ፡፡የታሸጉ ምግቦችን የሚያከፋፍሉ ሱፐር ማርኬቶች ለአመጋገብ ለውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድረገው ሊሆን ይችላል፡፡ ዶ/ር ክሪስ እንደዚህ ያሉ ምግቦች ለምንድነው የሚያጓጉን ብለው ይጠይቃሉ። ሱስ ሊያስይዙ ይችላሉ?

እነዚህ ምግቦች በልጆች አካላት ላይ የሚያስከትሉትን ውጤት የሚያሳዩ በክሊኒክ ላይ የተመረኮዙ ጥናቶች የሉም፣ ስለሆነም ዶ/ሩ በራሳቸው ላይ ለመሞከር ወሰኑ፡፡ለአንድ ወር ያህል 80 በመቶ የተቀየሩ ምግቦች በመመገብ፡፡
ዶ/ር ክሪስ በገዛ ራሳቸው ላይ ሙከራ በማድረግ ያዪት ውጤት አብረው የሚሰሩትን ሳይንቲስቶችን እንኳን በጣም ያስደነገጠ ሆኗል፡፡ዶ/ር ክሪስ አእምሮቸው እና አካላቸው ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ ልጆች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ የበለጠ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣው የህጻናት ከመጠን በላይ መወፈር እጅግ የተቀየሩ ምግቦች ዋና ምክንያት ሊሆን ይችላል ወይ በማለት በመጠየቅ ያጠቃልላሉ፡፡

Share this post

One thought on “ልጆቻችንን ምን እየመገብን ነው?

  1. ዋነኛ ጒዳይ አንስተሃል። በኢንቬስትመንት ስም ፒዛ ሃት ማክዶናልድ አስገብተን የአሜሪካኖችን አበሳ አብረን ልንበላ ነው! ህንድ አገር አበላላቸውን በቀየሩባቸው ሥፍራዎች ሁሉ በስኳር በሽታ፣ በደም ግፊት ወዘተ በአዳዲስ በሽታዎች እየተሰቃዩ ነው፤ በአገሪቱ ጤና አጠባበቅ ላይ ትልቅ ጫና ፈጥሯ። አሜሪካኖችና አውሮጳውያን የእኛን ምግብ ጥቅም ባወቁበት ዘመን የእነርሱን ዝባዝንኬ መለቃቀም እንዲያውም ያጠረ እድሜአችንን ማሳጠር ነው! ለአገርና ለሕዝብ የሚያስቡ ዜጎች ተሰባስበው መወያየት ይኖርባቸዋል።

Comments are closed.