ቀዳሚ ምኞቱ

ቀዳሚ ምኞቱ አራሽ መሆን ነበር። በወቅቱ መሬት ለባላባት እንጂ ላራሽ ስላልነበረ የቀለም ትምህርቱ ላይ ተጋ። ጊዜው ሲደርስ እርሻ ኮሌጅ ገብቶ ተመረቀ። ቤተሰብ ሲል፣ ሹመትና ዝውውር ሲል፣ አለቃ ሲጠምበት፣ ከተማ ለከተማ፣ ሚኒስቴር መ/ቤት ለሚኒስቴር መ/ቤት ሲንፏቀቅ፣ ከዚያ ለኮርስ ውጭ አገር፣ ልጅ ሲያስተምር፣ ለልጁ ሥራ ሲያፋልግ፣ ሲድር፣ አብዮት መጣ። መሬት ለመንግሥት እንጂ ላራሽ ሁሉ አይደለም ሲሉት፣ ልማታዊ መንግሥት መጣ። አሁን ቀናኝ ብሎ፣ በድብቅ ሲያስታምማት የኖረችውን የሙያ ፍቅሩን ቢቀሰቅሳት፣ በክልልህ የሚሉት መጣ። ለአንዳንዶች እንደ ሆነላቸው፣ ብሄሩ ሎተሪ ቀርቶ የሚሳቀቅባት ያልለየች ሰንካላ ዕጣ ሆነበችበት። በዚህ መሓል ጡረታህ ደርሷል መንገድ ልቀቅ ተባለ።

በማህበር ተመርቼ በማህበር ያሠራሁት ቤቴ ነው ክልሌ፤ ለኔ ገነት የዐፀዴ ሥፍራ ነው ብሎ በሩጫው ዓመታት ሎሚ ተክሎ ነበር። ግቢው የፈረስ ከንፈር ታክላለች፤ ግን እንደ ዐቃቢት መቀነት ብዙ ጒድ አሸክሟታል። የአበሻ ጎመን ካመት ዓመት አጥቶ አያውቅም፤ የአበሻ ጎመን ያለ ቃርያ ምን ያረጋል ብሎ ቃርያ ጨምሯል። ቡና ያለ ጤና አዳም፣ ክረምት ያለ በቆሎ፤ የበቆሎ ወዙ ዱባ። ወፎች እንኳ ከመሳፈርያቸው ጎራ ብለው እንደ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ፓርክ የሚያደንቊለት ሆነ።

ጡረታ ወጥቼ በየማኪያቶ ቤቱ ለምን ላውደልድል? አለ። ከጓሮ የጸሎት ምንጣፍ የምታክል ሥፍራ አበጃጅቶ ዘንጋዳ ዘራባት፤ ዘንጋዳዋ ጊዜዋን ጠብቃ ራሷን ቀና አደረገች። አንድ ቀን፣ ከዳር ያለችዋ ያማረባት ዘንጋዳ ተቀንጥሳ ወድቃ አገኘ። አንስቶ፣ ማ ቀነጠሳት? ከብት አይመስልም፤ ከብት በየት በኲል ገብቶ? ወፍም ሊሆን አይችልም፤ በምን አቅም? ሌላ ቀን ሁለት ራስ ከሥር ተመንቅረው ወዲያ ተጥለው አገኘ። ኮቴ ባይ ብሎ ላይ ታች አለ፤ እንኳ የወፍ የሰይጣንም ኮቴ የለም። አሽክላ አጠመደ፤ አሽክላው እስከ ዛሬ ምንም አልያዘም።

© 2021 by Mitiku Adisu. ፋቡላ ከንደገና፣ ገጽ 269—270. All rights reserved. መብቱ በሕግ የተጠበቀ ነው።

Share this post