አርትዩር ረምቦ
በፈዛዛ ወንዞች ላይ ወደታች ስናኝ
የመርከብ ሳቢዎቹ አመራር እንዳቋረጠ ተሰማኝ
ጫጫተኞቹ ቀይ ሕንዶች የለበሱትን ገፈው
ከቀለም ቅብ ግንድ ላይ እንደ ኢላማ አስደግፈው
አንድ ባንድ ለቀሟቸው።
የቤልጅክ ስንዴ የእንግሊዝ ጥጥ የተጫኑ መርከቦች
ሲጓዙ በአጠገቤ ሁሉንም አየኃቸው በቸልታ
የሳቢዎቹ ጭብጨባ አክትሞ ሲበርድ የቀያዮቹ ዋካታ
ጅረቶቹ አወረዱኝ ወደምፈልገው ቦታ።
ባለፈው ክረምት እንደ ሕፃን ቦዝ ሆኜ አእምሮ አልባ
ወደሚወራጨው ደራሽ ውሀ ተንደርድሬ ስገባ
የሚናወዙ ደሴቶች እንኳ እርስ በርሳቸው ሲምታቱ
በትርምሱ ድል እንደኔ አልተንገላቱ።
ማዕበል ባረከው የባህር ንቃቴን
ከደነገዘው ፋኖስ መራቄ ሳይነካው ስሜቴን
አሥር ሌሊት ሙሉ ከቡሽ በቀለለ ሁኔታ
ሰለባውን ጠቅላይ በተባለው ውሃ ላይ ስዳክር ቆየሁ ሳውታታ።
ልጅ እንዲረካ ሁሉ ጉምዛዛ ቱፋህ በጥርሱ እየጨመቀ
አረንጓዴ ውሀ የመርከቤን የጥድ ሣንቃ እየዘለቀ
ሰማያዊውን ነቢት ትፋቴንም አጽድቶ
ልጓምና ኩላቡን በታተነው አውጥቶ።
ከዚያማ ወዲያ በከዋክብት በተጌጠው ፍኖተ ሃሊብ በባህር ቅኔ ተዘፍቄ
አረንጓዴ አድማሳትን ስጠቀልል አጥብቄ፣
የገረጣ ተንሳፋፊ አስተያየቱ የቦዘዘ
በሃሳብ የተዋጠ ሬሳ አልፎ አልፎ በአጠገቤ ተጓዘ።
(Le bateau ivre የሠከረ መርከብ ከተባለው ግጥም ላይ በከፊል የተወሰደ ፤ ከፈረንሳይኛ ፡ ወደ ፡ አማርኛ ትርጉም ዶክተር ብርሃኑ አበበ)
ትርጉሙን በጣም ወድጄዋለሁ፣ የቀሩት ስንኞች ይቀጥላሉ ወይስ ይኸው ነው?