“ጀግና ነበር ብርሃነ መስቀል፡፡ ኢትዮጵያ የነበረችበትን ሁኔታ ከማንም ቀድሞ በመረዳት የዕሪታ ድምፁን በአደባባይ አሰማ፡፡ አስተማረ፣ ሰበከ፣ የተቃውሞ ሰልፍ መራ፡፡ ለለውጥ የተሰለፈ ጀግና ትውልድ አፈራ፡፡ ህልሙንና ዓላማውን ለማሳካት ኢሕአፓን በግንባር ቀደምትነት አቋቋመ፡፡ ሁለቱም ጀግኖች ነበሩ፡፡ ለየትውልዳቸው፡፡ ብርሃነ መስቀልና ጌታቸው ማሩ፡፡ ሁለቱም መሪዎች ነበሩ ለየትውልዳቸው፡፡ ሩቅ አሳቢና ዓላሚ፡፡ ለአገር ተቆርቋሪ፡፡ ብርሃነ መስቀል ጀግና ብቻ አልነበረም፡፡ አሳዛኝም (ፈረንጆች tragic hero የሚሉት) ነበር፡፡ የገነባውን ናደ፡፡ ኢሕአፓ ላይ ይህ ነው የማይባል ጉዳት አደረሰ፡፡ ከሁሉ በላይ ግን የመለመላቸውና ያስመለመላቸው ላይ መዓት እንዲወርድ ተባባሪ ሆነ፡፡ ግን ለምን?” (ኢትዮጵያ ሆይ! ክፍሉ ታደሰ ገጽ 259)
ከላይ የተጠቀሰው አንቀጽ ኢትዮጵያዊውን ፖለቲከኛ ብርሃነመስቀል ረዳን በሚገባ ይገልፀዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ (እንዲሁም በወቅቱ ለነበሩት የፖሊት ቢሮ አባላት ተመሳሳይም ባይሆን መሰል ጥያቄ ሊቀርብላቸው ይገባል፡፡ ፓርቲው ወደ ውድቀት ሲያመራ “ለምን ሌላ አማራጭ ስትራቴጂ አላዘጋጁም?” የሚልና መሰል ጥያቄዎች…) በዕርግጥም ብርሃነ መስቀል ለተገፉና ለተበደሉ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ጭቁኖች ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በአደባባይ ድምፁን ከፍ አድርጎ ጮኋል፡፡ ለዲሞክራሲ መብቶች መከበር፣ ለፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልና መሰል መብቶች መረጋገጥ ከፍተኛ ትግል አድርጓል፡፡ በዚህም የተነሳ በአፄ ኃ/ስላሴ መንግስት ለተደጋጋሚ እስርና ዕንግልት ተዳርጓል፡፡ በተለይም በ1957 ዓ.ም ብርሃነመስቀል ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስተባብሮ “የመሬት ላራሹ” መፈክርን አንግበው በአደባባይ እንዲጮሁ አድርጓል፡፡ ለዚህም ድርጊቱ ለተወሰኑ ዓመታት ከዩኒቨርሲቲ የትምህርት ገበታው ተባሯል፡፡ የመንግስት አፈና አላፈናፍን በማለቱ ብርሃነ መስቀል ከጓዶቹ ጋር በመሆን በ1961 ዓ.ም አውሮፕላን ጠልፎ መጀመሪያ ሱዳን ከዚያም አልጄሪያ ገብቷል፡፡ ከዚያም ከኢሕአፓ ምስረታ በኋላ የታጣቂ ቡድኑን አስኳል በኤርትራ በረሃ በኩል ይዞ በመሄድ አሲምባ ላይ አቋቁሟል፡፡ በኋላም በደርግ ተይዞ እስኪገደል ድረስ መሃል ኢትዮጵያ መርሃቤቴና መንዝ የታጠቀ ቡድን ይዞ ተንቀሳቅሷል፡፡ባለፉት ሰላሳ ዓመታት የዚያን ትውልድ በተመለከተ በተፃፉ መጻህፍት የብርሃነ መስቀል ስም ያልተነሳበት አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ አሁን ደግሞ ባለቤቱ ወ/ሮ ታደለች ኃ/ሚካኤል በቅርቡ አንድ መጽሐፍ አሳትማ ለገበያ አቅርባለች፡፡ የመጽሐፉ ርዕስ ዳኛው ማነው? የተሰኘ ሲሆን ከርዕሱ ስር “የብርሃነ መስቀልና የታደለች ህይወት በኢሕአፓ የትግል ታሪክ” የሚል አነስተኛ ንዑስ ርዕስ አለ፡፡ የመጽሐፉ ሽፋን ላይ ሁለት ፎተግራፎች ይታያሉ፣ የመጀመሪያው በቅርብ ዓመታት የተለቀቀው የብርሃነ መስቀል ጉርድ ፎተግራፍ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ታደለች ግራ እጇን አውጥታ የአሜሪካዋ የሲቪል መብት ተሟጋች የአንጄላ ዴቪስን መስሎ የሚታየው ነው፡፡የዛሬ ሰባት ዓመት ግድም ህይወት ተፈራ“Tower in the Sky”ን(ማማ በሠማይ) ፅፋ ለንባብ ስታበቃ ከኢሕአፓ መስራቾች አንዱ የነበረው ጌታቸው ማሩ በድርጅቱ ውስጥ የነበረውን ከፍተኛ አስተዋፅዖና የደረሰበትንም ችግር፣ የእሷንም የጎላ ድርጅታዊ ተሳትፎና በመጨረሻም በጌታቸው ማሩ ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ በውብ አተራረክ አቅርባልናለች፡፡ ብርሃነ መስቀል ረዳም ከመሰረተው ድርጅት ጋር ተመሳሳይ ችግር ውስጥ የገባ በመሆኑ ባለቤቱ ታደለች ኃ/ሚካኤል ከእርሷ ዕይታ አንፃር “መጽሐፍ ጽፋ ብቅ ትላለች” የሚል የብዙዎች ግምት ነበር፡፡ እንደተገመተውም አልቀረ፣ ታደለች ከላይ የተጠቀሰውን መጽሐፍ ፅፋና አሳትማ አቅርባለች፡፡የመጽሐፉ ሽፋንም ሆነ የውስጡ ወረቀት ተገቢውን ደረጃ ያሟላ ነው፡፡ ሽፋኑ ሲገለፅ የሚታየው የመጽሐፉ ርዕስ የፊደል መጠን (font) ያነሰ ይመስላል፣ ትንሽ ከፍ ቢል ጥሩ ነበር፡፡ በኮፒ ራይት ገጽ ላይ የሰፈሩት ፅሁፎች ጥሩ ሆነው ሳለ የአርታኢ ስም መፃፉ አግባብ አይመስለኝም፣ እንደዚህ ዓይነት ነገር ባይለመድ ጥሩ ነው፡፡ ማተሚያ ቤቱም ስልክ ቁጥሩን እዚሁ ገጽ ላይ ከማኖር ከጀርባ ወይም ሌላ ቦታ ቢፈልግለት የተሻለ ነበር፡፡ መጽሐፍና መጽሔት ይለያያሉ፡፡ ታደለች መጽሐፍ መፃፍ ያሰበችው ከአርባ ዓመት በፊት ወህኒ ቤት ውስጥ መሆኑን መቅድሙ ላይ ነግራናለች፡፡ ለምን እንደዘገየች የራሷ የሆነ ምክንያትን ባታቀርብልንም አሁን ግን በመፃፏ ተደስተን ምን አዲስ ነገር ትነግረን ይሆን በማለት ለማንበብ መጣደፋችን አልቀረም፡፡ በኢሕአፓ ድርጅታዊ ዕንቅስቃሴና በአባላቱም ተጋድሎ ዙሪያ እስከዛሬ ድረስ በርካታ መጽሐፍት ተፅፈዋል፡፡ የታደለችም ተዝቆ ከማያልቀው ታሪክ አንድ ተጨማሪ አስተዋፅዖ መሆኑ ነው፡፡ እኛም አንባቢያን ለተደረገልን ስጦታ ከልብ እናመሰግናለን፡፡ የኢሕአፓ ታሪክ መፃፉን ይቀጥላል፣ የእነዚያ ብርቅዬ ልጆች ተጋድሎና አኩሪ ታሪክ ለወደፊት በርካታ ዓመታት እየተፃፉና እየታተሙ ማንበባችንን እንቀጥላለን፡፡
ታደለች ኃ/ሚካኤል የመሃል አራዳ የፒያሳ ልጅ ናት፡፡ ሊሴ ገ/ማሪያም ትምህርቷን ጀምራ እተጌ መነን አጠናቃለች፡፡ ቤተሰቦቿም ከመካከለኛው መደብ ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉ ነጋዴዎች ሲሆኑ ፒያሳ መሃል ሱቅ ነበራቸው፡፡ ከመጀመሪያው የታደለች ነፍስ ለፖለቲካ የተጠራች አትመስልም ነበር፣ በዘመኑ ቋንቋም “ጆሊ ጃክ” ትመስላለች፡፡ የተማሪዎች መሪ ጥላሁን ግዛው ተገድሎ በተነሳው ረብሻ ተሳትፋ ከጓደኞቿ ጋር ጉዳት ደርሶባታል፡፡ ይህ ክስተት ግን ወደ ፖለቲካው እንድትሳብ ያደረጋት አይመስልም፡፡ አባቷ ዘወትር ይመክሯት የነበረው በርትታ ትምህርቷን እንድትከታተል እንጂ ፖለቲካ ውስጥ እንድትሳተፍ አልነበረም፡፡ የክርስትና ልጃቸው የጌታቸው ሃብቴ (በ1965 ዓ.ም ከእነ ዋለልኝ መኮንን ጋር ዓውሮፕላን ሊጠልፍ ሲል የተገደለ) በተማሪዎች ትግል ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን ምቾት ይነሳቸው ስለነበር አቶ ኃ/ሚካኤል ዘወትር ልጃቸውን ይመክሩ የነበሩት ትምህርቷ ላይ እንድትጠነክር ነበር፡፡
ታደለች የነፃ ትምህርት ዕድል አግኝታ ወደ ስዊዘርላንድ መሄዷን የምታበስረን ምዕራፍ ፩ መጀመሪያ ላይ ነው፡፡ “ዕለቱ እሁድ ህዳር 5 ቀን 1962 ዓ.ም…” ትላለች ታደለች ወደ ስዊዘርላንድ ለመሄድ ስትዘጋጅ፡፡ በተማሪዎች ረብሻ ምክንያት ክፉኛ የተሰላቹት አባቷ ወደ አውሮፓ ሊልኳት ተዘጋጅተዋል፡፡ “ህዳር 5 ቀን 1962 ዓ.ም” የሚለው ሃረግ ግን ትንሽ ውዥንብር መፍጠሩ አይቀርም፤ ምክንያቱም ገጽ 8 ላይ ታህሳስ 19 ቀን 1962 ዓ.ም ጥላሁን የተገደለ ዕለት አዲስ አበባ ውስጥ መሆኗንና ንቁ ተሳታፊም እንደነበረች ነግራናለች፡፡ ሆነ ብሎ ስህተት ፈላጊ ላለመባል እንዳጋጣሚ በስህተት የተፃፈ ነው ብለን እንለፈው፡፡ አንዳንድ አንባቢ ግን የታደለች የ8 ወራት የዩኒቨርሲቲ ህይወት ለምን ተዘለለ ብሎ መጠየቁ አይቀርም፡፡
ከአዲስ አበባ ስዊዘርላንድ ያደረገችውን ጉዞ በሚጠፍጥና ስዕላዊ በሆነ ድርሰት ነው የገለፀችልን፡፡ መጀመሪያ ዙሪክ ካረፈች በኋላ ቀጥላ ደግሞ ወደ በርን ሄዳለች፤ ከዚያ በኋላ ነው ትምህርቷን ወደምትከታተልበት ፍሪቡርግ ከተማ የደረሰችው፡፡ ጓደኛዋን ቅድስት ጎበዜን በማግኘቷ በባዕድ አገር ሊፈጠር ይችል የነበረውን ብቸኝነትና መደነጋገርን ለማስወገድ ችላለች፡፡ ብዙም ሳትቆይ ግን የምትኖርበት ከተማ ውስጥ በወቅቱ ፖለቲካ ንቁ ተሳትፎ ከሚያደርጉና በወደፊቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትግል መራር መስዋትነት ከከፈሉ ሁለት ግለሰቦች ጋር ትተዋወቃለች፣ እነሱም ተስፋዬ ደበሳይና አክሊሉ ህሩይ ናቸው፡፡ መጀመሪያ ላይ ሁለቱ ፖለቲከኞች ለሚያቀርቡላት የፖለቲካ ተሳትፎ ጥያቄ ምላሿ አሉታዊ ቢሆንም የኋላ ኋላ ግን መሳቧ አልቀረም፡፡ አውሮፓ ውስጥ በየጊዜው በሚካሄዱ የፖለቲካ ውይይቶችና ስብሰባዎች ውስጥ በመሳተፍ ንቃተ ህሊናዋን አዳብራለች፣ የትግል ስሜቷንም አሳድጋለች፡፡ ከአንጋፋው ፖለቲከኛና ከኢሕአፓ መስራቾች ውስጥ አንዱ ከሆነው ብርሃነመስቀል ረዳ ጋርም እዚያው አውሮፓ ውስጥ በተስፋዬ ደበሳይ አማካኝነት ተዋውቃ ይኸው ትውውቅ ወደ ፍቅር አድጎ ልጆች ለመውለድ በቅተዋል፡፡ብዙም ሳይቆይ የፖለቲካ ዕንቅስቃሴዋ ዳብሮ ለኢህአድ (የኢሕአፓ የመጀመሪያ መጠሪያ) አባልነት ተመለመለች፡፡ የመጀመሪያዋን ድርጅታዊ ግዴታዋንም የተወጣችው በ1966 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ወደ ኢትዮጵያ በመብረር ድርጅታዊ መልዕክት ለፀሎተ ህዝቅያስ እንድታደርስ በተስፋዬ ደበሳይ በተላከችበት ጊዜ ነበር፡፡ በመልስ ጉዞዋም ተመሳሳይ መልዕክት ወደ አውሮፓ ለእነተስፋዬ ደበሳይ አድርሳለች፡፡ኢህአድ (በኋላ ኢሕአፓ) በ1964 ዓ.ም ጀርመን ውስጥ ከተመሰረተ በኋላ ታጣቂ ክንፉን በ1966 ዓ.ም በብርሃነ መስቀል መሪነት ኤርትራ በረሃ እንዳስገባ ታደለች ተርካለች፡፡ እንደታሰበው ግን ታጣቂው የኢሕአሠ ጥንስስ ወደ ትግራይ አሲምባ አልዘለቀም፡፡ታጣቂው ቡድን ወደ አሲምባ የገባው በ1967 ዓ.ም አጋማሽ ከአንድ ዓመት ተኩል ኤርትራ በረሃ ውስጥ ከደረሰበት ዕንግልት በኋላ ነበር፡፡ እዚህ ላይ ታደለች ለብዙ አንባቢዎች አዲስ የሚመስል ዜና ይዛ ብቅ ብላለች፡፡ ይኸውም ኢሕአፓ ኤርትራን በተመለከተ ፕሮግራሙ ላይ ካሰፈረው አቋሙ በተፃራሪ “የኤርትራን ጥያቄ የብሔር ይሁን የቅኝ ግዛት ገና አቋም አልወሰድኩም፡፡ ለወደፊት የምመረምረው ይሆናል አለ” ያለችው ነው፡፡(ገጽ 169) ኤርትራ በረሃ ድረስ በመሄድ ይህንን የማይገባ ተግባር የፈፀሙትም ተስፋዬ ደበሳይና ዘርዑ ክህሸን መሆናቸውን ትገልፃለች፡፡ ይህንንም ጉዳይ በተመለከተ በ1969 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ታደለች ወደ ኢትዮጵያ በተመለሰችበት ወቅት ለተስፋዬ ደበሳይ አንስታበታለች፡፡ ነገር ግን ተስፋዬ ደበሳይ ተጨባጭ መልስ እንዳልሰጣት ተናግራለች፡፡በተጨማሪም ብርሃነመስቀል ስለ ተስፋዬ ደበሳይና ስለ ዘርዑ ክህሸን የነገራትን እንደሚከተለው አስፍራለች “ተስፋዬ ለትግሉ ከፍተኛ ከበሬታና ዕውቀት ቢኖረውም፣ በነበረው የትግል ልምድ ማነስ፣ በተለይም በተማሪው እንቅስቃሴ ያልነበረና ዘግይቶ የመጣ በመሆኑ ምክንያት፣ ዘርዑ የተስፋዬን ደካማ ጎን ተገን አድርጎ ተጠቅሞበታል፡፡ በተጨማሪም ተስፋዬ እጅግ ትሁትና የከተማ ጮሌነት የማይነካካው ሲሆን፣ በተቃራኒው ዘርዑ ምንም የሚገድበው አለመሆኑ፣ በንባብ የተደገፈ ዕውቀትን ለማዳበር ስንፍናም የተጫነው፣ መርህ የማይከተል፣ ቅፅበታዊ ድል የሚያስፈነጥዘው ወይ በአጭር ድል የሚረካ ነበር፡፡ ያቺን ድል ለማግኘት ያልሆነውን ቢሆን፣ ምን ይሉኛል የሚል ስሜት አልፈጠረበትም፡፡”(171)
እንደሚታወቀው ኢሕአፓ በ1967 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ታውጆ ፖለቲካዊ ዕንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ መጀመሪያ ግን የፓሪቲ መመስረቻ ኮንፈረንስ አካሂዶ ማዕከላዊ ኮሚቴውንና ፖሊት ቢሮውን ሰይሟል፡፡ ቀደም ሲል አውሮፓ ውስጥ በተቋቋመው ኢህአድ ውስጥ ብርሃነ መስቀል ዋና ፀሐፊና የፖሊት ቢሮውም አባል እንደሆነ ይታወሳል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው በኢሕአፓ የመመስረቻ ኮንፈረንስ ላይ ግን ለፓርቲው ፖሊት ቢሮ አባልነት ካለመመረጡም ሌላ የዋና ፀሐፊነቱም ቦታ ለዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ ተሰጠ፡፡ ታደለች መጽሐፏ ውስጥ በግልፅ ባታስቀምጠውም የብርሃነ መስቀልና የፓርቲው ግንኙነት መሻከር የጀመረው ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ይመስላል፡፡ተስፋዬ ደበሳይና ዘርዑ ክህሸን ለፖሊት ቢሮው አባልነት ተመርጠዋል፡፡ ታደለችም በ1969 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ወደ አገሯ ስለተመለሰች ድርጅታዊ ተሳትፎዋ ያን ያህል ጠንካራ አልነበረም፡፡ ብርሃነ መስቀል ረዳና ጌታቸው ማሩ ከፓርቲያቸው ጋር ልዩነት ፈጥረው የተለያዩበት ጊዜ ስለነበር ታደለችም ከፍተኛ ዕምነት ለሚጣልበት የሃላፊነት ወይም የስራ ቦታ ባትመደብ አይገርምም፡፡ብርሃነ መስቀልና ጌታቸው ከድርጅታቸው ጋር በፖሊሲ ጉዳዮች በሃሳብ ከተለያዩ በኋላ ሃሳባቸውን ከድርጅታዊ መዋቅር ውጭ ለሚያምኗቸው ጓዶቻቸው አሰራጩ፡፡ቁጥሩ ቀላል የማይባል የፓርቲው አባልም ተቀላቀላቸው፡፡ ከድርጅታቸው የተለዩባቸው ሁለት ዋና ዋና ነጥቦች የከተማው የትጥቅ ትግልና ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማሪያም ይወገዱ በሚለው ነው፡፡ ይህም ድርጊታቸው የፓርቲውን አመራር በማበሳጨቱ ሁለቱም ከፓርቲያቸው ተባረሩ፤ “በድርጅት ውስጥም ድርጅት መስርታችኋል” ተባሉ፡፡ በድርጅት ውስጥ ድርጅት ለመመስረታቸውም ታደለች መጽሐፉ ውስጥ አልፎ አልፎ ምልክት ሰጥታለች፡፡በታደለች ኃ/ሚካኤል የተፃፈውን “ዳኛው ማነው?” “የብርሃነ መስቀልና የታደለች ህይወት በኢሕአፓ የትግል ታሪክ” የሚለውን መጽሐፍ የሚያነብ ሰው ለማወቅ የሚጓጓው በዋነኛነት የብርሃነ መስቀልን ሁለተኛውን የታጠቀ ቡድን ምስረታና ያከናወናቸውን ተግባራት ነው፡፡ ብርሃነ መስቀል በ1969 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ታማኝ ጓዶቹን በመያዝና “ዱር ቤቴ” በማለት ወደ ሰሜን ሸዋ አቀና፡፡ ለትጥቅ ትግል የተመረጠውም ቦታ መርሃቤቴ ሲሆን “ታች ቤት መርሃቤቴ ዠማ ወንዝን አቋርጦ እጅግ ገደላማ የሆነውን አቀበት ከወጡ በኋላ በሚገኝ ጠፍጣፋማ ቦታ ላይ የነበረችው አምባ፣ በዠማ ፊት ሸዋ ሲሆነ፣ በወንጪት ፊት ከፍ ብሎ ወሎ ይወስዳል፡፡” (299) አካባቢውም ለሽምቅ ውጊያ አመቺ በመሆኑ ብርሃነ መስቀል ተዋጊ ቡድኑን በፍጥነት አደራጅቶ በአካባቢው ዕንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ የታጣቂ ቡድኑም ስም ታአአቡ (ታጥቆ፣ አንቂና አደራጅ ቡድን) የሚባል ሲሆን ብርሃነ መስቀልም ወደ አዲስ አበባ በመሄድ የቡድኑን ዕንቅስቃሴ ለተከታዮቹ አስረድቷል፡፡ታአአቡ ስሙን የሚወክል ተግባር ስለማከናወኑ ታደለች ምንም ሳትነግረን የብርሃነ መስቀል ቡድን መርሃቤቴ ውስጥ በተፈጠረ ህዝባዊ አመፅ የተነሳ ዓላማውን ማራመድ የሚያስችለው ዕንቅስቃሴ ማድረግ ስላልቻለ አካባቢውን በመልቀቅ ወደ መንዝ ተሰደደ፡፡ መንዝ እንደደረሰም መንግስቴ ደፋር ከሚባል የሽፍቶች ቡድን ጋር ተቀላቀለ፡፡ በወቅቱ በነበረው አስተሳሰብ ብርሃነ መስቀልን የመሰለ ዓለማ አቀፋዊ የግራ ፖለቲከኛ ከፀረ-ህዝብ የፊውዳል ቅጥረኞች ጋር መተባበሩ ቅር ቢያሰኝም አማራጭ ስላልነበረው ለተወሰነ ጊዜ አብሮ መቆየቱ ከረዥም ጊዜ ጥቅም አንፃር ጠቃሚ ሊሆን ይችል ነበር፡፡የብርሃነ መስቀል የታጠቀ ቡድን ወይም ታአአቡ መንዝ አካባቢ የረባ እንቅስቃሴ ሳያደርግ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከቆየ በኋላ “የእርማት ንቅናቄ” ተብሎ የሚታወቀውን የከተማ ክንፋቸው የሚገኝበትን ሁኔታ ለማጣራት ታደለች ወደ አዲስ አበባ ተልካ ግዳጇን ፈፅማ ተመልሳለች፡፡ በዚህ ወቅት የብርሃነ መስቀል ቡድን በመንግስት የስለላ ሃይሎች ተከቦ እንደሚገኝና በተለይ ገሠሠው የተባለው ሠላይ ከመንግስቴ ደፋር ጋር አብሮ መስራት ከጀመረ በኋላ ህልውናው አደጋ ላይ እንደወደቀ መጽሐፉ ፍንጭ ይሰጣል፡፡እዚህ ላይ የገጠሩ ታጣቂ ቡድን አዲስ አበባ ከሚገኘው ህዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ጽ/ቤት አባላት እንዳሉትና ከተማ ውስጥም ዕንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ በመጽሐፉ መጨረሻ አካባቢ እናነባለን፡፡ በወቅቱ ፖለቲካ ተሳተፊ ለነበረና ሁኔታውን ለሚያውቅ ሰው ደርግ እጅግ በጠነከረበት በ1971 ዓ.ም በአዲስ አበባና በአካባቢዋ በሚገኙ የገጠር አካባቢዎች ፀረ-መንግስት ዕንቅስቃሴዎችን ማድረግ በእሳት እንደመጫወት ያህል ነበር፡፡ ይባስ ብሎ የከተማው ቡድን የገጠሩን ክንፍ ለማጠናከር መሳሪያ ዘርፎ በታደለች መሪነት ወደ መንዝ ሲሄድ ወረኢሉ ላይ በመንግስት ሃይሎች ታገተ፡፡ ብዙም ሳይቆይ የብርሃነ መስቀል ቡድንም ምሽጉ ውስጥ እንዳለ ተከቦ ተያዘ፡፡ወደ መጨረሻው ላይ መጽሐፉ የብርሃነ መስቀል፣ የታደለችና የጓዶቻቸውንም የእስር ቤት ሰቆቃ ያትታል፡፡ በአጠቃላይ መጽሐፉ ተነባቢና እስከመጨረሻው እንዲያነቡት የሚያጓጓ ነው፡፡
ስለሺ ቱጂ ነሐሴ/2020 ዓ.ም
ቀዳማይ ምስል: ወ/ሮ እንጉዳይ በቀለ እና ወ/ሮ ታደለች ኃ/ሚካኤል በፈረንሳይ ቦርዶ ከተማ ጥቅምት/2019። ወ/ሮ እንጉዳይ በቀለ ስለኢሕአፓ ዘመን ትዝታቸው በፈረንሳይኛ « À l’ombre des eucalyptus», የሚል መፅሐፍ ፅፈዋል።
ጥሩ review ነው።ትንሽ ግራ ያጋብኝ ግን ፅሑፉ የሚጀምረው ክፍሉ ታደሰ ስለ ብርሃነ መስቀልና ጌታቸው ማሩ በሠጠው አስተያያት ነው።ክፍሉ ማለት ሁለቱ ከሞቱ በሗላ ኢሕአፓን ሲያሸከረክር የነበረ ሰው። በጌታቸው ማሩ ግድያ እጁ እንዳለበት በበርካታ ምስክሮች ተነግሯል።ብርሃነ መስቀልንም በጣም ይጠላው እንደነበር ራሱ ዜጋ መፅሔት ላይ ፅፏል። እና እንደ ነፃ እና መካከለኛ ሰው ስለ ሁለቱ ሰዎች አስተያየት ሲሰጥ እንዴት ሊታመን ይችላል?
Ato Tesfaye Makonnen, was a comrade-in-arms with the late Berhane Meskel Reda, diligently served Comrade Mengestou Hailemariam for 17 solid years. He also witnessed the imprisonment and the cruel death of this god-king. Similarly, like both these two revolutionaries, the late Nolawi Abebe and Getachew Maru became deadly enemies with each other after one joined the EPRP and, the other a gushing proponent of Anja. Here again, the widow of Berahane, Woizero Tadelech Hailemicheal Wakene served the nascent structure of Weyane for 27 years. Now, who is blaming whom based on whose moral authority? I guess one has to read with an open mind both books by Tesfaye and Tadelach, in order to understand the prevailing confusion that confounded this defrauded generation. Thanks for the fulsome review that discourages de haut en bas approach to the revolutionaries as disillusioned lost souls and political losers. Far from it, they have a lofty ideas and ideals to make Ethiopia a better place for everybody in the tumultuous 1970s. Cheers.