መንግስት እና የኃይል አጠቃቀም፤ የሕግ የበላይነት Vs ሥልጣን

ከልክ ያለፈም ትዕግስት፤ ከልክ ያለፈም የኃይል አጠቃቀም መንግስታዊ ባህሪዎች አይደሉም። አንዱ የመንፈሳዊ ሰው ሌላው የአፋኝ ቡድን ባህሪዎች ናቸው። ቀኝህን ሲመታህ ግራህን ስጠው የሚለው መንፈሳዊ አስተምህሮት የመንግስት ባህሪ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። መንግስት ቀኝ ሲመታ መቺውን በሕግ ጥላስር አውሎ ተጠያቂ ያደርጋል እንጂ ስለ ትዕግስት እያስተማረ ግራችሁን ስጡ ብሎ አይመክርም። በተቃራኒውም ቀኝህን የመታህን ቀኝ እጁን ቁረጠው ብሎም ከልክ ያለፈ እና ያልተመጣጠነ እርምጃም መውሰድ መንግስታዊ ባህሪ አይደለም። ወደ ፈላጭ ቆራጭነት ይወስዳል እንጂ።

የመንግስት ዋና ሥራ ሕግ ማስከበር፣ እንዳይጣስ መከላከል እና በተጣሰ ጊዜ አጥፊዎችን ሳይውል ሳያደር ይዞ ለፈጸሙጥ ጥፋት ተመጣጣኝ የሆነ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ ነው። በዜጎች ሞት እና ኪሳራ ትዕግስተኝነቱን እያሳየ የሰማይ ቤት ሊወርስ የሚዳዳው ወይም በፈለገ ጊዜ ከልክ ያለፈም እርምጃ እየወሰደ ስልጣኑን ሊያጸና የሚሞክር አካል የተረጋጋ አገር ሊፈጥር፣ ሰላም ሊያሰፍን፣ የሕግ የበላይነትን ሊያረጋግጥ እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ሊገነባ አይችልም።

የሕግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ከልክ ባለፈ ትዕግስት እና ከልክ ባለፈ ወይም ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃ መካከል አንድ ደሴት አለ። ይችን ደሴት መንግስት አንድም አያውቃትም አለያም ሆነ ብሎ ከአንድ ጫፍ ሌላ ጫፍ እየተስፈነጠረ ይዘላታል። ሕግ እና ጉልበት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ጉልበት በሌለብት ሕግ ጥርስ የሌለው አንበሳ ነው። ሕግ በሌለበት ጉልበት ብቻውን የሕገ አራዊት መገለጫ ነው። በየትም አለም መንግስት ወታደር፣ ፖሊስ፣ ደህንነት፣ ሚሊሻ ወዘተ … የሚሉ የኃይል አደረጃጀት የሚያስፈልገው ሕግ ለማስከበር፣ ሰላም ለማስፈን እና የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ነው። ትልቁ ጥያቄ ያለው በሕጎቹ ፍትሃዊነት እና በመንግስት የኃይል አጠቃቀም ላይ ያለው ሚዛን ነው። ያ ሚዛን ያለው ደግሞ ከልክ ባለፈው ትዕግስት እና ከልክ ባለፈው የኃይል አጠቃቀም መሃከል ባለው ደሴት ላይ ነው። ያ ደሴት ዜጎች በሰላም ውለው በሰላም የሚያድሩበት፣ ፍትሕ እና የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት፣ የመንግስት አካላት ላደረጉትን፣ ማድረግ ሲገባቸው ላላደረጉትም ነገር ተጠያቂ የሚሆኑበት ሥፍራ ነው።

በአንድ አገር የሕግ የበላይነት የሚረጋገጠው መንግስት በሕግ ተለክቶ የተሰጠውን የኃይል አጠቃቀም ሳይቀንስ እና ሳይጨምር በአግባቡ ሲጠቀምበት ብቻ ነው። የመንግስት የኃይል አጠቃቀም በሕግ ማዕቀፍ ልኬት የተበጀለት፣ ቁጥጥር የሚደረግበት እና ተጠያቂነት ያለበት ነው። ከልኩ በላይም ጉልበት መጠቀምም ሆነ ከልኩ በታች በትዕግስተኝነት ስም ጉልበት አለመጠቀም የሚያስከትለው ኪሳራ ስላለ መንግስትን ተጠያቂ ያደርጉታል።ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በተቃዋሚ ሰልፈኞች እና የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ በመንግስት የኃይል አጠቃቀም ላይ ያስተዋሉትን ግድፈት እና ስጋታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ የክልሉ መንግስት እና በማህበራዊ ድህረ ገጽ ሃሳባቸውን በነጻነት በመግለጽ የሚታወቁት አቶ ታዮ ደንደአ የኮሚሽኑንን መግለጫ በማጣጣል ተቃውሟቸውን ገልጸዋል። የክልሉ መንግስትም ሆነ አቶ ታዮ የተቃውሟቸው ማጠንጠኛ ሃሳብ መንግስት ዝም ሲል ሕግ አላስከበረም ብላችው ትወቅሳላችሁ፤ እርምጃ ሲወስድ ደግሞ ያልተመጣጠነ ትላላችሁ የሚል ነው።ይህ ሙግት የአብይ አስተዳደር ስለ ሕግ የበላይነት እና ሕግን በጉልበት ስለማስከበር ያለውን የከረመ የአስተሳሰብ ግድፈት ዛሬም ይዞ መቀጠሉን የሚያሳየው ነው። መንግስት ባለፉት ሁለት አመታት በተለይም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ይከሰቱ ከነበሩ ጥቃቶች፣ ዘርና ኃይማኖት ተኮር ጭፍጨፋዎች፣ ንብረት ዝርፊያ እና ውድመት ጋር ተያይዞ ይወቀስ የነበረው እነዚህ ድርጊቶች ሲፈጸሙ የዳር ተመልካች በመሆኑ ነው። መንግስት በዚህ አገር ውስጥ አለ ወይ እስኪባል ድረስ በቀላሉ ሊቆሙ እና በቁጥጥር ስር የሚውሉ የሕገ ጥሰቶችን ከዳር ቆሞ እያየ ለቅሶ ደራሽ ነበር። በዚህም አገሪቱን ቀላል የማይባል በሰው ሕይወት እና ንብረት ዋጋ አስከፍሏታል። ምንግስት ይህን ክስተት የትዕግስተኛነቱ ማሳያ እያደረገ በማቅረብ ሊወደስበትም ሲዳዳው ታይቷል። ለደረሱት ውድመቶች እና ግድያዎች ተጠያቂው ማነው? መንግስት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ስንወተውት ጠቅላዩን ጨምሮ የመንግስት አካላት ስለ ትእግስተኝነት ያወሩ ነበር። ዜጎች በጠራራ ጸሃይ በጭካኔ ሲገደሉ እና የግለሰቦች ንብረት ሲወድም ትእግስተኛ የሚመስለው የአብይ አስተዳደር አጥቂዎቹ ፊታቸውን ወደሱ እና ወደ መንግስት ሥልጣን ሲያዞሩ ደግሞ ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ ጉልበቱን ሲፈትሽ እና የተነጣጠረበትን ጥቃት በፍጥነት ሲያከሽፍም በተደጋጋሚ ይስተዋላል።

ይህ የሚያሳየው መንግስት ሕግን ለማስከበር የሚያስችል በቂ ኃይል ያለው ቢሆንም ኃይሉን የሚጠቀመው ዜጎችን ከጥቃት ለመከላከል ሳይሆን ሥልጣኑን እና የባለሥልጣኑን ደህንነት ለማስጠበቅ ብቻ እንደሆነ ነው። ወደ እኔ አትምጡ እንጂ እርስ በርሳቸው ያሻችሁን ሁኑ ያለ ይመስላል። ለእዚህ አቶ ታዮ ደንደአ የኮሚሽኑን መግለጫ በተቹበት ጽሑፋቸው ትላንት ብዙ ጉዳት ያደረሱት ጽንፈኛ አካላት ዛሬ ደግሞ የብልጽግና አመራሮችን እና ቤተሰቦቻቸው ላይ እርምጃ ለመውሰድ በአደባባይ ማወጃቸው እየታወቀ እና ለዛም እየተንቀሳቀሱ እንዴት የኃይል አርምጃ አንጠቀምም ብለው ሽንጣቸውን ገትረው ይሞግታሉ። ስለዚህ እራሳችንን ለመከላከል የምንወስደው እርምጃ እንዴት ክልክ ያለፈ የኃይል እርምጃ ተደርጎ ይቆጠርብናል ብለዋል።

አቶ ታዮ ደንደአ ያለማፈራቸው ትላንት እገሌ የተባለው አክቲቪስት ለዚህን ያህል ሰው ሞት ምክንያት ሆኗል፣ እገሌ ይህን በማድረጉ በመቶዎች የሚጎጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፣ ዛሬ እኛን ሊገድሉን ስለሆነ ዝም ብለን እንጠብቅ ወይ የሚል መከራከሪያ ነው ያቀረቡት። ቡና የለም እንጂ ቡናማ ቢኖር እንደተባለው ፍትህ የለም እንጂ ፍትህ ቢኖር ኖሮ አቶ ታዮ ትላንት ያሁሉ ሰው እሳቸው በሚያስተዳድሩት ክልል ውስጥ በግፍ ሲጨፈጨፍ ምንም አይነት ፈጣን ምላሽ ባለመውሰዳቸው ከነባልንጀሮቻቸው፤ ጠቅላዩን ጭምሮ ዳኛ ፊት በቀረቡ ነበር።

የመንግስት ሥልጣን ላይ ተፈናጦ አገር እያስተዳደሩ ዜጎች የጥቃት ሰለባ ሲሆኑ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ አደጋውን ከማስቆም እና አጥፊዎችን ለፍርድ ከማቅረብ ይልቅ ፌስቡክ ላይ ወጥቶ እንጉርጉሮ ማሰማት ከመንግስት ባለሥልጣን የሚጠበቅ ተግባር አይደለም። ትላንት በማንም ቀስቃሽነት ይሁን ሰዎች በጠራራ ጸሃይ ሲገደሉ እርሶና መንግስትዎ ምን እየሰራችው ነበር? የመንግስት ያለህ ድረሱልን ሲባል ‘የማሪያም ብቅል እየፈጨሁ ነው’ የሚል መልስ እንኳ ያልሰጣችሁ ሰዎች ዛሬ በእናንተ ዝምታ ለደረሰው ጉዳት ሁሉ ቁጥር እየጠቀሱ አጥፊዎቹ ላይ ጠአት መጠንቆል አሁንም የመንግስት ኃላፊነት የገባቸው አልመሰለኝም። ሕግ አስከብሩ፤ ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃ አትውሰዱ።

Share this post