በ 40ዎቹ ና በ 50ዎቹ ዘመናዊ ሙዚቃ፣ ፉሽን ና የምሽት ህይወት አዲስ አበባ ውስጥ በተለይ አራዳ አካባቢ ሲያብብ፥ ከዚያ ጋር ተያይዞ ስማቸው በዋናነት ይጠቀሱ ከነበሩት መካከል ሜሪ አርምዴ አንዷ ነበረች። በወቅቱ የገነነ ስም ቢኖራትም፥ ስለእርሷ የተፃፉ ብዙ መረጃ ማግኘት አዳጋች ነው።ይህንን እውነታ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ቀጣዩን መነን መፅሔት መጋቢት 1965 የታተመ ፅሑፍ እዚህ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ አትመንዋል።ፅሑፉ ከአርቲስቷ ጋር በተደረገ ቃለመጠይቅ ላይ ተመርኩዞ የተፃፈ ሲሆን የፀሓፊው ስም አልተጠቀሰም።የመፅሔቱ ሥራ አስኪያጅ ግን ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ነበር።
እኔ መጀመሪያ አርቲስት ለመሆን የመረጥኩት ገና ትንሽ ልጅ ሆኜ ነው።የተወለድኩት አራዳ ጊዮርጊስ ነው። በሠፈራችን መደዳውን ጠጅ ቤት ነበር።ዘውትር ይዘፈናል። እኔም የታዘዝኩትን ትቼ ወደዚያው ሄጄ ቀስ ብየ እያሾለኩ በመጋረጃ ውስጥ እመለከታለሁ።የዚያን ጊዜ ዘፋኞቹ እነ ባፈና ወልዱ፥ ንጋቷ ከልካይ፥ እነ ጥሩ ብርቄ ነበሩ።እነሱኑ በመመልከት ስሜት ያዘኛና አንጐራጉር ጀመር።ሰውም “ነይ እስቲ ሜሪማ ዝፈኝልን” ይለኛል።ያኔ ስሜ ሜሪማ ነበር። የአራዳ ሴቶች መሪ ከሆንኩኝ በኅላ ስሜን ሜሪ ብየ ቀየርኩት።አባቴ ጐንደሬ እናቴ ራያ ናቸው።እነሱ ናቸው ሜሪማ ብለው ስም ያወጡልኝ።
ይኄውልህ አርቲስት ለመሆን የነበረኝ ስሜት ከዚያን ጊዜ ነው የጀመረው።በጠላት ጊዜ እንኳ ምንም ልጅ ብሆን፥ ይባል የነበረውን ሁሉ አንጐራጉር ነበር።
ሜሪ አርሚዴ ፋቄ የሚባል ሀገር ሁለት ዓመት በስደት ኖራለች። በኃላም የፋሽስት መንግስት “መንኩሴዎች ፥ህፃናት፥ደካሞች ተመለሱ” ብሎ ሲያውጅ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰችና እዚያው ቀድሞ ሠፈሯ አራዳ ገባች።ሜሪ ስትናገር “ዘመዶቼ ሙያ እንዳውቅ በይ ፍተይ፥ ስፌት ስፊ” ሲሉኝ አሻፈረኝ እያልኩ ማንጐራር ብቻ ሆነ።ነጋ ጠባ እገረፋለሁ።እኔ ግን አንዴ በዚህ ተለክፌያለሁና ውሎየ ጠጅ ቤት ሆነ።ቤተዘመድ ተሰብስቦ መከረና ሚሲዮኖች ዘንድ ሄጄ እንድማር ተደረገ።እዚያም ሄጄ ትምህርቱ አልሆነልኝም።ማንጐራር ሆነና መምህራኑን አስቆጣቸው።በኃላም ይህቺ ልጅ ዘፈን እንጂ ትምህርት አይሆናትም፥ ደህና ልጆችን መጥፎ ትምህርት ታስተምርብናለች ብለው ትምህርት ቤቱን እንድለቅ አደረጉ። ዘመዶቼም ተናደው እንደገና እዚያው ትምህርት ቤት አንጠልጥለው ወሰዱኝና ጫጩትም ቢሆን እዚሁ ትምህርት ቤት ሆና ትጠብቅ እንጂ እቤት ውላ ጠባይዋ ሊሻሻል አይችልም ብለው የትምህርት ቤቱን አስተዳዳሪ ለመኗቸው።እርሳቸውም የቤተሰቦቼን መጨነቅ አይተው ለሁለተኛ ጊዜ ተቀበሉኝ። ሜሪማ እንደሆንኩ አሁንም ሀሳቤ እዚያው ጠጅ ቤት ነኝ።ጓደኞቼ ከመፅሐፍ ጋር ሲታገሉ እኔ አንጕራጉራለሁ። የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ የነበሩት መነኩሴ ተበሳጭተው ሁለተኛ ዓይኗን እንዳላይ ብለው አባረሩኝ።የትምህርቴም ነገር በዚሁ አከተመ።
አራዳ ጊዮርጊስ ከሚገኙት ጠጅ ቤቶች ከሚገኙት ጐራ እያልኩ መዝፈኔን ቀጠልኩ።ከጊዜ በኅላ ከአንዲት ፈረንሳዊት ጋር ተዋወቅሁ።ከእርሷም ጋር ፍቅራችን የጠና ሆነ።በዘመኑ ብርቅ የነበሩትን ዳንሶች አጠናሁ። በዚሁ ሙያዩ ሰው ሁሉ ጉድ አለ።ያን ጊዜ በውስጥ ሱሪና በጡት መያዣ፥ በባዶ እግር ነበር የሚደነሰው።ታዲያ ይህ ጉዳይ ሕብረተሰቡን አስቆጥቶት ነበር።ፈረንሳዊቷ ወደ ሀገሯ ስትገባ ንብረቷን ለኔ አስረከበችኝ።ከዚያም አሁን የሞዳኖቫ ሱቅ ከተሠራበት የራስ ኃይሉ ንብረት ላይ ይገኝ የነበረ ቤት በከፍተኛ ገንዘብ ተከራየሁ። ችግሬ ግን የሠለጠኑ ሴቶች ማግኘቱ ነበር።እንዳሁኑ ሴቶች እኔው መርጬ አሠለጠንኳቸው።የፀጉር አሠራሩንም፥ ዳንሱንም አሠለጥንኳቸው።በዚያን ጊዜ ዳንሱም አለባበሱም ብርቅ ስለነበረ ገበያው ደራ።የዚያን ጊዜው ደንበኞቼ ሁሉ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ደርሰዋል።ተጫዋቾቼም ጥሩ ቦታ ላይ ነው ያሉት።ግማሾቹ ትልልቅ ቡና ቤት ከፍተዋል። ሌሎቹ ደግሞ ባለቪላ ሆነዋል።ይህንን መቼም ሁሉ ያውቀዋል። ለጉራና ራሴን ከፍ ለማድረግ አይደለም፣እነሱም አልፎ አልፎ ይጠይቁኛል።እኔ ሳላሰልጥናቸው በፊት በየጣሰው ቤት ክራራቸውን ይዘው ኩር ኩር ያደርጉ ነበር።ያኔ ከሰል ተራ ወይም ቺንኮ ተራ ይሉታል።ቺንኮ የሚሉት ጣሊያኗች ነበሩ።ስሙኒ ማለት ነው።እኛም ወዲያም ወዲህ ብሎ ይበላል ቆንቂቲ አድባሯም ጥሩ ቢያፈራንም ኬቲ እያልን ስለ ከሰል ተራ እንጫወት ነበር።ታዲያ እኔም ሴቶቹ አሳዘኑኝና “ምን ትሠራላችሁ? ቆንጆ ናችሁ፥ታምራላችሁ።ኑ እኔ ጋ ዳንሱን ተማሩ።እኔ ቤት ስንቱ እንግሊዝ፥ ስንቱ አሜሪካ፥ ስንቱ መኳንንት ይመጣል።እኔ ልውሰዳችሁ።”ስላቸው “እኛ ልብስ የለንም። አንቺ ጋ መጥተን ምን እንፈጥራለን?” ሲሉኝ “ግድ የለም።የኔ ጌጥ የኔ ልብስ አለ።” እያልኩኝ እወስዳቸው ነበር።እዚያው ፀጉራቸውን እየተኮስኩ፥ ኩሉን እየኳልኩ አሳመርኳቸው።ዳንሱንም በደንብ አስተማርኳቸው።
ወይዘሮ ሜሪ ያለፈውን ጊዜ በማስታወስ “ይኸውላችሁ እነሱኑ ለማሠልጠን ስል የፀጉር መተኮሻውን ካስክ (ቆብ) እራሴ ላይ እያደረግሁ በሽተኛ ሆንኩ።” አለች።ቀጠል አድርጋ ዘወትር ቅዳሜና እሁድ የኔን ቤት ያየ ግራ ይገባዋል።የሰው ብዛት ይህ ነው አይባልም።ረብሻ እንዳይፈጠር ሰባት ዘበኛ ነበረኝ።
ገና በጊዜ “አርቲስቶቹ ገቡ ወይ በስንት ሰዓት ነው ዳንሱ የሚጀምረው?” እያሉ ስልክ ይደውላሉ።ልክ ሦስት ሰዓት ሲሆን ቤቱ በሰው ይሞላል።በኅላም አርቲስቶቹ የውስጥ ሱሪና የጡት መያዣ ብቻ ለብሰው ብቅ ይላሉ።
አስቀድመን ዊሲኪ ጠርሙስ ውስጥ ትንሽ ዊሲኪ እናደርግና በሻይ እንበርዘዋለን።ቦዩን በደንብ አስጠንቅቄ ከሌለው መጠጥ ጋር አብሮ ይደረድረዋል።ሴቶቹም ሲጋበዙ ዊሲኪ እንዲሉና ሻዩን እንዲጠጡ አድርጋችዋለሁ።ይህንን የማደርግበት ምክንያት ተሳክረው ዳንሱን እንዳያበላሹት ነው።
ወንዶቹም ሴቶቹ አንድ ጠርሙስ ዊሲኪ ለሦስት ጠጥተው ለምን አይሰክሩም እያሉ ይደነቃሉ።ለመቅመስ ሲመጡም ቦዩን ጠቀስ እናደርጋውና በምትኩ ሌላ ጠርሙስ ያኖራል።ይህን የምናደርገው ሞቅ ካላቸው በኃላ ነው።
የዳንሱም አይነት የበዛ ነው፤ ታንጐ፤ ቫልስ፥ ቤርዲሉና፥ ማዙካ፥ ቲፕታፕ፥ እነዚህን ሁሉ እንጫወት ነበር።ቤርዲሉና የተባለው ዳንስ ወንድና ሴት እቅፍቅፍ ብለው ፍቅራቸውን የሚወጡቡት ነው።ዳንሱም የሚመራው በአረንጓዴ መብራትና በለስለሳ ሙዚቃ ነው።ማዙካ በውርርድ የሚጫወቱት ዳንስ ነው።በሻምፓኝ፥ በወርቅና በገንዘብ እየተወራረዱ ጫወታሉ።እኔ ከዳኞቹ አንደኛዋ ስለነበርኩ ፊት ለፊት እንቀመጥና ለረታው ሽልማቱን እንሰጣለን።
ለመጀመሪያ ጊዜ ቀይ መብራት እሥራ ላይ ያዋልኩ ነኝ።እቤቴ ውስጥ የነበረው የመብራት አይነት ብዙ ነበር።ሁሉም ከየአቅጣጫው ፏ ብሎ ይበራል።የውጭ አገር ዜጐችማ ልክ የአገራቸውን እየመሰላቸው ይደነቁ ነበር።ይህንን ቀይ መብራት ዛሬ በየመንደሩ ተንጣሎ ሳየው በጣም ያናደኛል።ያኔ እንዴት ያምር ነበር።አትክልቴ ውስጥ ሳይቀር እንኳን መብራት አደርግ ነበር።ታዲያ አሁን ሁሏም አንጠልጥላው ሳይ ያስቀይመኛል።በመጀመሪያ የተጠቀምኩበት እኔ መሆኔን የሚውቁ እግዜር ይይልሽ አንቺ ባትጀምሪው ኖሮ እኛም አንጠቀምበትም ነበር።አሁን ይኸው ለስድብ አዋልሽው እያሉ ይወቅሱኛል።
በኅላም ይህ ነገር በጣም እየተለመደ በመሄዱ አንዳንድ ሰዎች ተጋሩኝ። ማዘጋጃ ቤትም ፈፅሞ በውስጥ ሱሪና በጡት መያዣ ብቻ እንዳይደነስ ጥብቅ ትዕዛዝ አወጣ።ስለዚህም ረዥም ልብስ፥ ከላይ ክፍት የሆነ ብቻ ይለበስ ጀመር።ይህ በመጠኑም ቢሆን ገበያዬን ቀንሶብኛል።
እያደር ብዙ ሰዎች ቡና ቤትና ዳንስ ቤት ከፈቱ።ረብሻውም እየበረከተ ሄደ።ከተማው ውስጥ ድብድብ ሆነ።ስሞታውም በዛብኝ።ትኰራለች፥ሰው ትጠየፋለች እያለ ጐረምሳው ይዝትብኝ ጀመር።እኔም ልክ እንደሙሽራ እደበቅ ነበር።ይህቺ ሜሪ የሚሏት የቷ ናት እያለ ሁሉም ይወራረዳል።እኔ የምደበቅበት ምክንያቱ እኔን ለማየት ብቻ ገንዘባቸውን እየከፈሉ የሚመጡ ሰዎች ስለነበሩ ነው።መንግስት ሳይሾመኝ ልክ እንድ አንድ ሚኒስተር በአራዳ ውስጥ አዝ ነበር።
ቅድም እንደተናርኩት እያደር ንትርኩ ጠቡ በመብዛቱ ትንሽ ተበሳጨሁ።ይህንንም ሥራ ለማቆም ወሰንኩ።ሠራተኞቼም እራሳቻችንን እንቻል ስላሉኝ ዳንስ ቤቱን ዘጋሁ።
ሌላ የገቢ ምንጭ ማግኘት ፈለግሁና ወደ ፀጉር ሥራው አተኰርኩ።ይህንንም ሥራ ለመጀመር ያነሳሳኝ አንድ ትልቅ ሰው ቤት ግብዣ ተጠርቼ ሄጄ የጋባዤ ልጅ ነጠላ ተከናንባ በአጠገቤ ስታልፍ ማየቴ ነው።በጣም ነደደኝ።ምክንያቱም ቆንጆ ሆና ሳለ በነጠላ ተከናንባ ውበቷን ስላጠፋቸው ነው።ፈረንሳይቷ ጓደኞዬ የፀጉር ሥራ አስተምራኝ ስለነበረ ሱቅ ከፍቼ ይህንን ሁሉ ቆንጆ የባሰ ማስዋብ አለብኝ ብዬ ወሰንኩ።የኛ ሴቶች ፀጉር እንደምታውቀው በደንብ የተያዘ አይደለም።ይህን አምበሬ ጭቃ ይለድፉና በዚህ በአበሻ ሚዶ ሲያበጥሩት ለጥ ብሎ ይተኛላቸዋል።አዳር ቤት ሲሄዱ የሰው አንሶላ ያጨማልቃሉ።በነሱ ቤት መሠልጠናቸው ነው።እኔም እየተመለከትኩ በግጥም እሰድባቸው ነበር።
ያሠራሽው አልጋ ወፍራም አጣና ነው፥
ያነጠፍሽው ፍራሽ የሱሉልታ ሣር ነው፥
እግርሽ ከታጠበ ሰባት አመቱ ነው፥
የጠጉርሽ አቧራ ዓይኔን ሊያጠፉው ነው
እያልኩ እነሱን በማንቋሸሽ ሥራዬን አስተዋወቅሁ።በዚህም ብዙ ደንበኞች አፈራሁ።የቻሉት ያኔውኑ ይሰጡኛል።ያልቻሉት ቀስ በቀስ እዳቸውን ይከፍላሉ።በዚህ ብዙውን አሠለጥንኩ።ብዙዎችም ጐፈሬአቸውን እንድከረክምላቸው ይለምኑኛል።ያኔ ወንዶቹም እንዲህ እያሉ ይገጥሙ ነበር።
ጐፈሬ ክም ክም ጐፈሬ ክም ክም ጫማ ሲጥ ሲጥ
እኔ አላገባሽም ምኒልክ ይሙት፤
አየህ የዚያን ጊዜ ጐፈሬ አንድ ሰዓሊ ተጨንቆ የሳለው ነው የሚመስለው።የዛሬውማ የዛር ውላጅ ይመስል ተንጨፍሮ ማስቀየሙ።የያኔው ሌላ ነው።በርሞሌ የሚባል ሽቶ ስለነበር እሱንም እሸጥ ነበር።
ካፒቴን ናልባንዲያን ነፍሳቸውን ይማረውና- ዲያቆኖችንና ድምፀ መልካሞችን አንድነት ሰብሰብው ያሠለጥኑ ነበርና፥ እኔንም በዳንሱና በልብሱ በኩል ነይና እርጂን ስለአሉኝ ማዘጋጃ ቤት ተቀጠርኩና ለአክተሮቹ የልብስ ሞድ በማቅረብ አገለገልኩ።ከዚያም ቀዳማዊ ኅይለ ሥላሴ ቴያትር ተዘዋውሬለዘጠኝ ዓመታት አገለገልኩ። የቴዎድሮስ ቴያትር ሲሠራ ሹሩባውን፥ አንዳንዱን ጌጥ፥ የሃኒባል ቴያትር ሲሠራ ልብሱን ያዘጋጀሁት እኔ ነኝ።ይሁን እንጂ እያደር ባየው የደመወዝ አበል ሳይሰጠኝ በነፃ ይህን ያህል ጊዜ ማገልገሌ ቅር አለኝ።በእርግጥ ቤቱ ብዙ ነገር አስተምሮኛል።ይህንን አልክድም።
ሜሪ ይህን ያህል ጊዜ ስትኖር የሕግ ባል እንደነበራት ለጠየቅናት መልስ ስትሰጥ “አንድ እንግሊዛዊ አግብቼ ነበር።ስሙ ጁሮምሉ ይባላል።ከእርሱ ጋር ብዙ ጊዜ ኖሬአለሁ።ግን ልጅ አልወለድንም።በመሀሉ ያቺ ፈረንሳዊት ወደ ጂቡቲ ይዛኝ ሄደችና ትዳሬ ፈረሰ።የማልዘነጋው ነገር ቢኖር የጁሮምሉ ሁኔታ ውለታ ነው።አልፈልግም ብዩ ወደ ጂቡቲ ስሄድ ብዙ ገንዘብ ሰጠኝ።ከዚያ ወዲህ ዓይን ዓይን አልተለያየንም።ከእርሱ ያፋታኝ ዋና ምክንያት የሰው አፍ ነው።ሜሪ ሐይማኖቷን ለወጠች እያሉ ሲያወሩብኝ እርግፍ አድርጌ ተውኩት።
ሜሪ አርምዴ ይህን ያህል ዘመን ስትኖር ምንም ቅርስ አላፈራችም። ሜሪ ያልሞከረችው ሥራ አልነበረም።ቀድሞ አራዳ ውስጥ ዝናዋ ያስተጋባውን ያህል ዛሬ በአንዲት አነስተኛ ቤት ተወስና የጥቂት ደንበኞቿን ፀጉር ትተኩሳለች።አልፎ አልፎ በሬድዮ ድምፅዋ ሲሰማ ፥ በቴሌቪዢን መስኮት ብቅ ስትል ብቻ አይ ሜሪ የሚሉ የጥንት ወዳጆቿ ናቸው።እሱዋም በአሁኑ ጊዜ ከክራርዋ አብልጣ የምትወደው የላትም።ክራርዋ ከራስጌዋ በዥጉርጉር ቀለም ዘንጦ ተሰቅሏል።ሲከፋት ከተሰቀለበት አውርዳ ዘፈኗን ትነካዋለች።ባሌም፥ አባቴም ወንድሜም ክራሬ ነው የምትለው ሜሪ መከፋቷ እንዲታወቅባት አትፈልግም።ዘውትር መሳቅ ነው።ይሁን እንጂ በሕይወቷ ቅር የሚያሰኝ ዱብዳ አንድ ቀን የደረሰባት መሆኑን አወጋችኝ።
“ይኸውልህ ድህነቴን እያወቁ ጋዜጠኞቼ ጉድ ሠሩኝ።ውጭ ሀገር ያሉ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ከፍ አድረገው ዝናየን ለሚርያም ማኬባ ነግረዋት ነበር አሉ።ስማችሁም መልካችሁም ይመሳሰላል።ትልቋ የኢትዮጵያ አርቲስት እርሷ ነች።”ብለው ስለነገሯት እሷም እኔን ለማየት ትፈልግ ኖሮ፥ ለአፍሪካ ስብሰባ በመጣች ጊዜ ጋዜጠኞቹ እዚያች ደሳሳ ጐጆየ ይዘዋት መጡ።
ድሃ ነኝ ገንዘብ የለኝም በያት አሉኝ።እኔ ለራሴ ጥዩፍ ነኝ።እኔ ለራሴ ጥዩፍ ነኝ።ደሀ ነኝ ብላት ምናልባት አንድ ሺህ ብር ወይንም ያነሰ ነው የምትሰጠኝ።ግን ዞራ አይ የኢትዮጲያ አርቲስት ብላ ማለቷ አይቀርም።ለምን ልዋረድ? ሚርያም ማኬባ በቱርጅማን “ቤትሽ እዚህ ነው?” አለችኝ።ሰውነቴ ሽምቅቅ አለ።ምክንያቱም ጥቀርሻው፥ ሸረሪቱ እንኳ እንኳን ለእሷ ለሌላውም አይበጅ።ቶሎ አልኩና “የለም የኔ ቤት ይህ አይደለም ። ገረዴ ታማ ልጠይቃት መጥቼ ነው”። አልኩ።ገረዴ ሳትታመም በብርድ ልብስ ጀቡኜ አልጋ ውስጥ አስተኟኃትና እንድታቃስት ለመንኳት።እሷም እንዳልኳት ኧኧኧ ስትል ሚርያም ማኬባ አዘነችና አምሳ የአሜሪካን ብር አንስታ “እንቺ ስጫት” አለችኝ።እኔም ያቺን ብር “የኔ ገንዘብ ነው በኃላ ትሰጭኛለሽ”። ብዬ ትራስዋ ሥር አስቀመጥኩ።በኃላም ቤትሽን አሳይኝ ብትለኝ ቀዳማዊ ኀይለስላሴ ቲያትር አጠገብ ያለውን የበድሉን ሕንፃ የኔ ነው ብዬ ነገርኳት።ለቱርጁማኑ እናትና አባቴ ስለርስት ጉዳይ ንትረክ ይዘዋልና ፀትታ እነነሳቸዋለን።እሁድ እራት ጋብዤሻለሁና እንዳትቀሪብኝ።አልኩና ተሰናበትኳት።ግብዣውን የት አባቴ እንደማዘጋጅ ግራ ገባኝ።ምን ይዋጠኝ? ምነው ያችኑ አነስተኛ ቤት የኔ ነች ባልኩ ፥ እያልኩ ስጨነቅ አንድ የማውቃቸውን ከፍተኛ ስልጣን ያላቸውን ሰው ላስቸግር ወሰንኩ።እቤታቸው ሄጄ እግራቸው ላይ ወድቄ አለቀስኩ።ታሪኩንም ዘርዝሬ ነገርኳቸው።እሳቸውም በነገሩ ተደንቀው፥ ደግሰው፥ቤቱን በደንብ አድረገው አዘጋጁልኝ።ከዚህም ሌላ ሚርያም ማኬባን ከሆቴሏ የሚመጣት መኪናና ሾፌር ሰጡኝ።እኔም የእሳቸውንና የባለቤታቸውን ፎቶግራፍ ከግድግዳው ላይ አንስቼ የኔን ፎቶ አደረግሁ።የራሴ ቤት ለማስመሰል ፒጃማ ለበስኩ።ልክ እንደቤቴ ሽር ጉድ እያልኩ ጋበዝኳት።ሾፌሩንም አስቀድሜ ለምኜው ነበርና ከእራት በኅላ እሷን ለማድረስ ስንወጣ ወርዶ እጅ ነስቶ፥ መኪና ከፍቶ አስገባን። ሆቴላም ስንደርስ ሮጦ ወጣና ከፈተለን።
በመጨረሻም የሀገር ልብስ ጥሩውን በርካሽ ዋጋ ገዝቼ ሸለምኳት።እሷም ቆንጆ የደረት ጌጥ ሸለመችኝ።እባክህ ጌታዬ አታጋልጠኝ ብዬ ለቁልቢው ገብርኤል ጥላና ጧፍ ተስዬ ነበር።ሳልጋለጥ ቀረሁ እልሃለሁ።
ባይልልኝ ነው እንጂ እኔም ቢጠሩኝ የማልሰማ እመቤት ነበርኩ፤ምን ያደርጋል እጄ አመድ አፋሽ ሆነ።”አለች እንባዋ አቅሮ መሬቱን እየቆረቆረች።
ብስጭቴን፥ ምሬቴን፥ ችግሬን ፍቅረኞቼን የማስታውሰው ከክራሬ ጋር ስሜት ሲይዘኝ ነው።አለችና ክራሯን ደረደረች።
እስቲ ጠይቁልኝ ሚስቲቱን በሰው፣ ባሏ ልቤን ወስዶ የት አደረሰው?
ዛፍ ያጣ ጉሬዛ አዳኝ ያበረረው የማትሆነኝ እንደሁ ልቤን ተው ልበለው
ጐጃምና ጐንደር ማዶ ለማዶ ነው ፍቅር ያለቦታው አባ ጨጓሬ ነው።
ዋይ ብዬ ልለይህ ዘመድ እንዳረዱት፥ ሰቀቀን ነውና የሩቅ ሰው ቢወዱት
ተበድዬ ኑሬ አንጀቴ ተቃጥሎ
አንጀቴ ተቆርጦ
ስቃጠል ከርሜ
ዳግሚያ ሰው ወደድኩኝ ልብ የለኝም እኔ።
ወዘፍዘፍ ያለ ነው የግራር አጥር፥
እኔ ለጅል ፍቅር እምብዛም አልጥር
ሸህ አባድር መጀን አምስቱ በረኛ፥
አዙሮ አዙሮ ይጣልህ ወደኛ።