ከኮቪድ ጋር በተያያዘ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያኖች ላይ እየደረሰ ያለው እንግልት

የሠላሳ ዓመት ጕልማሳው የሆነው አቶ ተመስገን ሃንኮሬ፥ በደቡብ አፍሪካ በምትገኘው በካርስዴል ከተማ ነዋሪ ነው። ወደ ደቡብ አፍሪካ ከመጣ ሰባት አመት የሆነው ሲሆን ከባዶ ተነስቶ ባደረገው ከፍተኛ ጥረት የራሱን ሱቅ አቋቊሞ የሚተዳደር ነው። አቶ ተመስገን ገና ትዳር ያልያዘ  ቢሆንም ፥ ከሱቁ በሚያገኘው ገቢ እራሱን ከማስተዳደርም አልፎ ፥ ሆሳዕና የሚገኙት ቤተሰቦችን በገንዘብ ይደግፋል።በመላው አለም የተሰራጨው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በአፍሪካ ውስጥ ክፉኛ ካጠቃቸው አገሮች መካከል ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ነዋሪ በመሆኑ በሺታው የንግድ ዕንቅስቃሴው ላይ ተፅዕኖ አሳድሮበታል።

ወረርሽኙ መሰራጨት ሲጀምር፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሙሉ ውሸባ (lockdown) ውስጥ ገብታ የነበረ ሲሆን አሁን ደረጃ በደረጃ፣ እየተነሳ ይገኛል። ተመስገንም፣ደረጃ 3 ሲታወጅ፣ ከወር በፊት፣ ከማዘጋጃ ፍቃድ ወስዶ፣ ሱቁን ከፍቷል።ነገር ግን አሁንም በሚሸጣቸው ዕቃዎች ላይ ገደቦች አሉበት። አገሪቱ ባወጣችው ደንብ መሰረት ለምሳሌ ሲጋራ እና የሺሻ (flavor) ምርቶችን መሸጥ አይፈቀድለትም።ይሁንና ተመስገን የተዳከመውን ገቢውን ለማስተካከል በሚያደርገው ጥረት እነዚህ ምርቶች ተፈላጊ በመሆናቸው ያለ ፈቃድ ሲሸጥ በመገኘቱ፣ለአንድ ቀን ታስሮ ተለቋል። 1000 የሀገሬው ገንዘብ ራንድም እንዲከፍል ተወስኖበታል። ይህ ሁሉ ችግር ቢገጥመውም ተመስገን መደበኛ ሥራውን ሳያስተጓጉል ይሠራ ስለነበር ከገቢ አንጻር ብዙ አልተጐዳም ነበር። በጆሃንስበርግ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ግን ብዙ ችግር እንደደረሰባቸው ሰምቷል።በርካቶች ስራቸውን አጥተዋል፤ ገሚሶቹም የሚሸጡትን ዕቃዎችን ለገበያ ማዋል ሳይችሉ ቀርተዋል።

ተመስገን ሃንኮሬ

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያኖች ከከሚደርስባቸው ችግሮች አንዱ ከቤት ኪራይ ጋር በተያያዘ ገቢያቸው በመቀነሱ መክፈል ባለመቻላቸው ነው። በህጉ መሠረት፣ የቤት መቀመጥ ህግ በታወጀበት ወቅት ፣ ተከራዯችን አከራዮች ማስወጣት ባይችሉም፤ በአከራዮቻቸው ተገደው ከቤት እንዲወጡ የተደረጉ እንዳሉ ፤ወይም እንዲወጡ በተዘዘዋሪ ጫና ፣ለምሳሌ የመብራት መስመርን በማቋረጥ፣ እንደሚደርግባቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ።ነዋሪዎቹ እንደሚሉት በመጀመሪያው እና በሁለተኛው ወር፥ አከራዮች ሲታገሷቸው ቢቆዮም ሦስተኛው ወር ላይ ግን ጫናው ከፍ እያለ መጥቷል።ችግሩ የከፉ በመሆኑ በአንዳንድ ጉዳዪች በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ፣ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲው ጣልቃ ለመግባት እንደተገደደ ፤ ነዋሪዎች ተናገረዋል። በጆሃንስበርግ ከ 20 ዓመት በላይ የኖረው አብራሃም ተፈሪ እንደሚለው፣ ቤት ኪራይ መክፈል ባለመቻላቸው፣ ተባረው ቤተክርስትያን የተጠለሉ ቤተሰቦች አሉ። የተባበሩት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማህበር እንዲሁም ሀበሻ ኮሚኒቲ ፕሪቶሪያ የኢትዬጵያውያን ማህበረስብ በደቡብ አፍሪካ ቤተሰቦቹን ለመርዳት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ አብራሃም ለኢትዮጵያ ኦብሰርቨር ተናግሯል።

የደቡብ አፍሪካው የቤት የመቀመጥ ትዕዛዝ ጥብቅ ቁጥጥር የነበረበት ስለነበር ሰዎች ከቤት ለመውጣት ባለመቻላቸው፥ በተለይ የዝቅተኛ ገቢ ተዳዳሪዎች ፥ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠዋል። የደቡብ አፍሪካ መንግስት ለሀገሬው ሰዎች የነፃ የምግብ ዕደላ ቢያደርግም በሀገሩ የሚኖሩ ስደተኞችን ግን ችላ እንዳለ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ይናገራሉ። “በመርህ ደረጃ፥ የደቡብ አፍሪካ ወረቀት ያላቸው ሁሉ፥ የምግብ ዕደላውን የማግኘት መብት አላቸው። ችግሩ ግን ብዙ ስደተኞች ህጋዊ ወረቀት የላቸውም። በዚህ ምክንያት፥ ምንም አይረዱም,” ይላሉ በጆሃንስበርግ የሚገኘው የአፍሪካ የስደተኞች እና ማህበረሰብ ማዕከል (The African Centre for Migration & Society) የተሰኘው ተቋም ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ሎረን ላንዶ።

ቁጥራቸው ከ 3.6 ሚሊዮን በላይ፥ የውጭ ሀገር ዜጐች የሚኖሩባት ደቡብ አፍሪካ ፥ህጋዊ ወረቀት የሌላቸው ስደተኞች፥ የገቢ ምንጫቸው ነጥፏል። በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት የተለያዩ ማህበራት ዕገዛ ለማድረግ የሞከሩ ቢሆንም መንግስት ግን ዕገዛውን ለዜጐቹ ብቻ አድርጏል።

እንደሚታወቀው፥ደቡብ አፍሪካ ከስደተኞች ጋር ያላት ግንኙነት እጅግ የተወሳሰበ ነው። በተለይም ጥቁሮች በሚኖሩባቸው ታውንሺፖች፥በውጭ ሀገር ዜጐች ላይ ጥላቻዎች ይንፀባረቃሉ፤ ጥቃቶችም ይደርሳሉ። የኮቪድ መከሰተም ነገሮችን ያባባሰው ይመስላል። በኮቪድ ጊዜ፥ ከስራቸው በተሰናበቱ እና ተስፋ በቆረጡ የሀገሬው ሰዎች የሚደርሱ፤ ጥቃቶች ተጠናክሮ እንደቀጠሉ ፥ በዚያው ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያኖች ይናገራሉ። አንዳንዴም ጥቃቶቹ የሚፈፀሙት በፀጥታ አካላት ነው። ለአብነት ያህል ከሁለት ቀን በፊት ፥ ፀጥታ ሃይሎች በካዋ ዙሉ ናታል ፕተርማስበርግ ከተማ በተኮሱት ጥይት ሰላሙ ተስፉየ የተባለ አንድ ኢትዮጵያዊ ሕይወቱ ሲያልፍ በሌሎች አምስት ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል። United Media House ለተባለ በኢትዮጲያኖች ለሚመራ ሚዲያ ምስክርነታቸውን የሰጡ የአይን እማኞች እንዳሉት፥ ፖሊሶቹ ለዝርፊያ ሆን ብለው የመጡ እና የፖሊስ መኪናቸውን ራቅ አድረገው በማቆም ወደ ሱቆች በመግባት እዚያ የነበሩትን ሰዎች መሬት ላይ እንዲተኙ በማዘዝ፥ ለመዝረፍ ሲሞክሩ ኢትዮጵያኖቹ በመቃመዋቸው፥ የተኩስ እሩምታ ተከፍቶባቸዋል። Xenowatch የተባለ በስደተኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች የሚመዘግብ ድርጅት እንደሚለው ሐምሌ 10 ላይ በኬፕታውን Philippi በተባለ ታውንሺፕ፥ አንድ ሶማሊያዊ እራሱ ሱቅ ውስጥ ተገድሎ ተገኝቷል።ከሳምንት በኅላም፥ ሁለት ሶማሊያውያን ባለሱቖች እና አንድ የማላዊ ዜጋ ሰራተኛቸው ላይ ተተኩሶባቸዋል።ሁለት ሶማሊያውያን ሕይወታቸው አልፏል። “ይሄ እንደማስጠንቀቂያ ነው። እዚህ የተደራጁ አካላት ለሶማሊያ ስደተኞች እያስተላለፉ ያሉት መልዕክት፥ ደህንነታቸሁን ለማስጠበቅ መክፈል አለባችሁ የሚል ነው።» ይላል ሲሊንዲሌ ምሊልሎ የተባለ የ Xenowatch ባልደረባ።

Share this post

One thought on “ከኮቪድ ጋር በተያያዘ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያኖች ላይ እየደረሰ ያለው እንግልት

  1. በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ስደተኞችን ሁሉተስፋ እንዳጡ አድርጐ ማቅረብ ስህተት ነው።አብዛኛዎቹ የተሰካላቸው የሚባሉ ናቸው። የራሳቸውን business run ያደርጋሉ።ኮቪድ ሲጀምር እና የቤት መቀመጥ ህግ ሲታወጅ አዋጥተው በችግር ያሉ የደቡብ አፍሪካ ዜጐችን ረድተዋል። ይሄ መረሳት የለበትም።

Comments are closed.