አንቺን ሲልሽ ሲልሽ… እንዳይሆን የመንግስት ነገር፤

ሰውየው አጥብቆ የሚፈልጋትን የልብ ወዳጁን እሱ በፈለጋት ጊዜ ፈልጎም አያገኛትም፤ እሷ በፈለገችው ጊዜ ደግሞ ድንገት ከች ትላለች። በዚህ የተበሳጨው አፍቃሪ ታዲያ እንዲ ብሎ ገጠመ ይባላል፤ አንቺን ሲልሽ ሲልሽ ትመጫለሽ በእግርሽ፣ እኔን ሲለኝ ሲለኝ የትም አላገኝሽ።በአገሪቱ የሕግ የበላይነት ከጠፋ ከሁለት አመታት በላይ ተቆጠሩ። በዘር ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ጨምሮ እጅግ ከፍተኛ የመብት ጥሰተችም ባሳለፍናቸው አመታት ውስጥ ተፈጸሙ። ዜጎች በየመንደሩ በጠራራ ጸሃይ ታረዱ። በድሃ አገር ብዙዎች ለዘመናት አንጀታቸውን ቋጥረው ያፈሩት ሃብትና ንብረታቸው በወሮበሎች ተዘረፈ፣ በእሳት ጋየ።የኛም ያለ መታከት የፍትሕ ያለ እያልን ስንጮኽ ሰሚ አልነበረም። በስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ለርስ በርሱ ግጭት በቂ ትኩረት አለመስጠታቸው እና ፍትሕን ማስከበር አለመቻላቸው እጅግ ቢያሳዝነኝም ብዙዎች እንደሚያስቡት ግን የመንግስት ዝምታ ከአቅም ማነስ ነው የሚል የተሳሳተ አረዳድ ኖሮኝ አያውቅም። መንግስት ግጭቶቹን ለማስቆምም ሆነ አጥፊዎቹን ለመቆጣጠር ከና ከጠዋቱም በቂ አቅም እንደነበርው እገምታለሁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ጊዜ ለተከሰቱት የእርስ በርስ ግጭቶች እና በሦስቱ ሰኔዎች በተከሰቱት ወንበር ነቅናቂ ጥቃቶች ያሳዩት ምላሽ የመንግሥታቸውን ባህሪ በደንብ ያሳብቃል። ሕዝብ ሲጫረስ እና ዜጎች የጥቃት ሰለባ ሲሆኑ መግለጫ ለመስጠት እንኳ ከራርመው ነው ብቅ የሚሉት። መግለጫቸውም ግልጽነት ያልነበረው እና አገም ጠቀም የሆነ ነበር። ነገርየው ወደ ወንበር ንቅነቃ ያመራ የመሰላቸው ጊዜ ደግሞ የሲቪል ልብሳቸው አውልቀው ጥለው እና የወታደራዊ ልብስ ለብሰብ ሳይውል ሳያድር በቴለቪዥን መስኮት ብቅ ሲሉ አይተናል። ለዚህ ሦስቱ ሰኔዎች ጥሩ ምስክር ናቸው። በሦስቱ ሰኔዎች ጠቅላዩ የወታደር ልብሳቸውን ለብሰው ብቅ በማለት ቁጣቸውን አሳይተዋል። በቡራይ እልቂት፣ 86 ሰዎች ባለቁበት የጥቅምት ግጭት እና በሌሎችም ተመሳሳይ የጎንዮሽ ግጭቶች ጠቅላይ ከራርመው እና በሲቪል ልብሳቸው ሆነው፤ አንዳንዴም የዛሬዎቹን አጥፊዎች ‘እስኮርቴ’ እያሉ እያሞጋገሱ ነገሮችን ሲያደባብሱ ታዝበናል።

ዛሬ ግን ግጭቱ ከእርስ በርስ መናቆር አልፎ በሥልጣን የመቆየት ዋስትናቸውንም የሚያናጋበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ሹማምንቱ ከእንቅልፋቸው ባነውና በርግገው የተነሱ መስለዋል። ለዛም ነው ሰውየው ሲፈልጋት እንደማትገኘው ሴትዮ እኛ ስለ ፍትሕ ስንጮኽ አናገኛችሁም፤ አደጋው የእናንተን መንደር ሲያንኳኳ ግን የሲቪል ልብሳችሁን ጭምር አውልቃችው ጥላችሁ በየቀኑ መግለጫ በመግለጫ የምታንበሻብሹን። በዚህ እና ሌሎች ተመሳሳይ ምክንያቶች መንግስት አሁንም የሕግ የበላይነትን የማስፈን እና ሰብአዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር ሥራውን ከልብ ሊይዘው ነው ወይስ የተነሳውን የተቃውሞ ማዕበል ለማስተንፈስ ብቻ ከመተለም የሚል ስጋት የገባኝ። ሰሞኑን ብዙ የሰቆቃ ዜናዎች እየሰማን ነው። በተለይም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚኖሩ እና ኦሮሞ ባልሆኑ ኢትዮጵያዊያን ላይ እየተፈጸመ ያለው በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት አዲስ ነገር ባይሆንም በሰማነው ቁጥር ልብ ያደማል፣ ይሰቀጥጣል፣ ያሳፍራል፣ ያስቆጫል፣ የመንግስት ያለህ ያስብላል። በተለይም በአማራ፣ በወላይታ፣ በጉራጌ እና በጋሞ ተወላጆች ላይ ባለፉት ሁለት አመታት በክልሉ ውስጥ ተከታታይ ጥቃት ሲፈጸም ቆይቷል። ይህ አዲስ ነገር አይደለም። በተለይም በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የደረሰውን ሰቆቃ ለማሰብ ይከብዳል። አንድ ቤተሰብ ሙሉውን በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለባቸው ክስተቶች ብዙ ናቸው። አንዳንዶቹን ጥቃቶች የሚያሳዩ የፎቶ እና የቪዲዮ ምስሎችም እየደረሱን ነው።እነዚህን ጥቃቶች ባየሁ ቁጥር፤ እንዲህ አይነቱን የአውሬነት ተግባር የሚፈጽሙት ወጣት ልጆች አይምሯቸው ውስጥ ምን አይነት ጥላቻ እና ልክፍት ቢኖር ነው? ምን ብለው ቢነግሯቸው ነው? እነዚህስ ወጣቶች ነገ ምን አይነት ህይወት ነው የሚኖራቸው? የዚችስ አገር እጣፈንታ ምንድን ነው የሚሆነው እያልኩ ከራሴ ጋር እሟገታለሁ። አንድ ሰው እንዲህ አይነት ጭካኔ የተሞላው ተግባር በራሱ ወገን ላይ እንዴት ሊፈጽም ይችላል? እንዲህ አይነት መጥፎ ተግባራት በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎችም መጠኑ ይነስ እንጂ ተደጋግሞ ተፈጽሟል። በተለይም በኦሮሚያ ክልል ትንሽ ኮሽ ባለ ቁጥር ሜጫቸውን ስለው የሌላ ብሔር ተወላጅ ወደሆነ ጎረቤታቸው የሚሮጡ ወጣቶች ባለፉት ሁለት አመታት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመግለጽ በሚሰቀጥጥ ሁኔታ አካላቸውን እየቆራረጡ ገድለዋል። በድሬዳዋ፣ በሐረር፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በሻሸመኔ፣ በናዝሬት፣ በዝዋይ፣ በጅማ፣ በቡራዩና በአዲስ አበባ አጎራባች መንደሮች እና በወለጋ ይህን መሰል ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ተደጋግሞ ተፈጽሟል።

ካችአምና ለኦነግ አቀባበል ሲደረግ፣ ትላንት ጃዋር ተከበብኩ ሲል፣ ዛሬ ደግሞ በግፍ የተገደለውን የአርቲስ አጫሉን ሞት ሰበብ በማድረግ በመቶዎች የሚቆጠሩ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ የሌሎች ብሔር ተወላጆች ደም በጠማቸው ግፈኞች እጅ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። የመንግስት ታጣቂዎች በአንዳንድ አካባቢዎች ጥቃቱን ለማስቆም በወሰዱትም እርምጃ ሰላማዊ ሰልፈኞች የጥቃት ሰለባም የሆኑበት ክስተት ተፈጥሯል። የአብይ አስተዳደር ላለፉት ሁለት አመታት ይህ ሁሉ መከራ በሕዝብ ላይ ሲወርድ ጆሮውን ደፍኖ ለቅሶ ደራሽ ነበር። የፍትህ ያለህ እያልን ደጋግመን ስንጮህ ታዛቢ እንጂ ሰሚ አልነበረንም። እንደውም አንዳንዶቹ አደጋዎች ከመድረሳቸውም በፊት ምልክቶች ይታዩ ስለነበር ለመንግስት በአደባባይ ማሳሰቢያዎችን እየሰጠን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ እና ዜጎች ለተመሳሳይ ጥቃት እንዳይጋለጡም ድምጻችንን ስናሰማ ቆይተናል። ሰሚ ግን አልነበረም።

በዚህ ሦስት እና አራት ቀናት ውስጥ የወንድማችንን የአጫሉን ግድያ ተከትሎ መንግስት ወገቡን ጠበቅ አድርጎ አጥፊዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የተዘጋጀ መሆኑን እና ትግስቱም ተሟጦ ያለቀ መሆኑን ባለሥልጣናቱ ደጋግመው ነግረውናል። እሰየው ነው፤ በስተመጨረሻም ቢሆን የዜጎችን ጥቃት ለማስቆም እና አጥፊዎችን ለፍርድ አቅርባችው ተጠያቂ ለማድረግ ከልብ ወስናችው ከሆነ የሚበረታታና የሚደገፍ እርምጃ ነው። እሱን እንግዲህ እያደር የምናየው ይሆናል። የእኔ ስጋት መንግስት አሁን እየወሰደ ያለው የጅምላ እርምጃ ለሕግ የበላይነ ከመቆርቆር፣ በማንነት እና በዘር ላይ ያነጣጠረው የዜጎች መጠቃት እና እልቂት አሳስቦት ወይስ የመጣው አደጋ ከዘር ፍጅት አልፎ የአገዛዙን የሥልጣን ዘምንም የሚያሳጥር መዘዝ ይዞ ስለመጣ ይሆን? የሚል ነው። ይሄንንም እያደር የምናየው ይሆናል።መንግስት ባላፉት ጥቂት ቀናት የተቀሰቀሰውን የሕዝብ ቁጣ ለመቆጣጠር በሚል በወሰደው እና እየወሰደ ባለው እርምጃ ላይ አንዳንድ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ነገሮች ቢኖሩም አገሪቱን ወደ እርስ በርስ ግጭት ሊከቱ ዝግጅት አድርገው እና ተደራጅተው በመንቀሳቀስ አጫሉን ከመግደል አልፎ ወደ ዘር ተኮር እልቂት ያመሩትን ተጠርጣሪ ሰዎች እና አስተባባሪዎች በሕግ ጥላ ስር ማዋሉ ያስመሰግነዋል እንጂ አያስወቅሰውም። ተጠርጣሪዎቹ ንጹ ሆኖ የመገመት መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በተጠረጠሩበት የወንጀል አድራጎት ተይዘው ምርመራ እንዲካሄድባቸው መደረጉ ግን ከመንግስት የሚጠበቅ እርምጃ ነው። ከዚህ በኋላ አገሪቱን ከማረጋጋት ጎን ለጎን መንግስት ሊወስዳቸው የሚገቡ ነገሮች ግን ያሉ ይመስለኛል፤+ በሕግ ጥላ ስር የዋሉት ሰዎች ተገቢው የሕግ ጥበቃ ተደርጎላቸው፣ ጉዳያቸው በአፋጣኝ ተመርምሮ እና ማስረጃዎች ተሰባስበው ወደ ክስ ሂደት የሚያመሩትን መክሰስ፣ በቂ ማስረጃ ያልተገኘባቸውን ሰዎች በዋስትና ወይም በነጻ መልቀቅ፣+ ከተፈጠረው ሁከት ጋር ምንም አይነት ንክኪ የሌላቸውን ነገር ግን የመንግስት የፖለቲካ ተቀናቃኝ የሆኑ ግለሰቦች በዚህ ግርግር ውስጥ ኃላፊነት በማይሰማቸው ሹማምንት የጥቃት ሂላማ እንዳይደረጉና በሰበብ አስባቡ እንዳይታሰሩ፣ በጸጥታ ኃይሎች ወይም በተዋረድ ባሉ የመንግስት አካላት ወከባና ጥቃት እንዳይደርስባቸው ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ፣+ ይህን ግርግር ሽፋን በማድረግ የፖለቲካ ተቀናቃኛቸውን ለማጥቂያነት ሁኔታውን መጠቀሚያ ባደረጉ የመንግስት አካላት ላይ ተገቢውን ክትትል አድርጎ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ፣+ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚኖሩ እና የጥቃት ሰለባ ለሆኑ የሌሎች ብሔር ተወላጆች መንግስት ተገቢውን ጥበቃ እና ለወደመውም ንብረታቸው ማካካሻ የሚሆኑ ድጎማዎችን ማድረግ፣ ቤት ለተቃጠለባቸው የመኖሪያ ቤት ማመቻቸት፣ የንግድ ቤቶቻቸው ለወደሙባቸውም ሰዎች ድጋሚ ሊቋቋሙ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ እንዲሁም ከጥቃቱ ሸሽተው በየመጠለያው ላሉ ሰዎች ለደህንነታቸ ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ፣+ ተመሳሳይ እና ዘር ተኮር የሆኑ ጥቃቶች በኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች እንዳይቀሰቀሱ እና ዜጎች አደጋ ላይ እንዳይወድቁ፤ እንዲሁም ይህ አይነቱ የእርስ በርስ ግጭት እያደር ከቁጥጥር ውጭ ወጥቶ አገሪቱን ወዳልተፈለገ እልቂት እና ትርምስ እንዳይከት ከወዲሁ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እና ጥንቃቄ ማድረግ፣+ በስተመጨረሻም፤ በየጊዜው ደጋግሜ የማነሳው የአገራዊ መግባቢያ፣ እርቅ እና ፍትህን ማዕከል ያደረገ የብሔራዊ ምክክር መድረክ ሳይውል ሳያድር ማካሄድ፣ + ባለፉት ሁለት አመታት በኦሮሚያ ክልል፣ በአማራ ክልል፣ በቤኒሻንጉል ክልል፣ በደቡብ ክልል፣ በድሬዳዋና በሐረር የተፈጸሙ የጅምላ ጭፍጨፋዎች በገለልተኛ መርማሪዎች እንዲጣራ ማድረግ ይኖርበታል።በስተመጨረሻም+ በዘር ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች በአፋጣኝ ይቁሙ!+ መንግስት የጀመረውን የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባር ጥንቃቄ በተሞላው እና ሕጋዊነቱን ባለቀቀ መልኩ አጠናክሮ ይቀጥል!+ ክስተቱን ለሌላ የፖለቲካ አጀንዳ ማሳኪያ ወይም የስልጣን ማራዘሚያ ተደርጎ በመንግስት ሹማምንት እንዳይወሰድ ጥንቃቄ ይደረግ!+ መንግስት በፖለቲካ ፓርቲዎች እና አመራሮች ላይ የሚወስዳቸውን አላስፈላጊ እርምጃዎች መልሶ ያጢን፤ እርምጃ መወሰድም ካለበት በበቂ በማስረጃ እና በሕግ ብቻ የተደገፈ ይሁን!

Share this post

One thought on “አንቺን ሲልሽ ሲልሽ… እንዳይሆን የመንግስት ነገር፤

  1. “በአገሪቱ የሕግ የበላይነት ከጠፋ ከሁለት አመታት በላይ ተቆጠሩ።” ያሬድ ኃ/ማርያም
    አቶ ያሬድ ኃ/ማ ድብን ያለ እንቅልፍ ወስዶት መሆን አለበት! ሄሎ! አቶ ያሬድ፣ ህወሓት የሚባል ነበረ። አሁን ሸሽቶ መቀሌ መሽጓል! ሃያ ሰባት ሲገዛ ነበረ።

    ቀጥሎ “ሰውየው አጥብቆ የሚፈልጋትን የልብ ወዳጁን እሱ በፈለጋት ጊዜ ፈልጎም አያገኛትም” ይለናል አቶ ኃ/ማ። ድብን ያለ እንቅልፍ ወስዶት እንዴት ያግኛት? ያ ሰው ኃ/ማ ራሱ ነው!

Comments are closed.