ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ የቀበር አፈጻጸም ሁኔታና ከአንድ የጸጥታ አባል መገደል ጋር በተያያዘ ፖሊስ ከሌሎች ሰዎች ጋር አስሯቸዋል የተባሉት የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ (ኦፌኮ) አባላት ማዕከላዊ ውስጥ እንደሚገኝ ፓርቲያቸው ገለጸ።
“የፓርቲያችን አባላት የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ ሐምዛ ቦረና በተዘጋው ማዕከላዊ ታስረው ይገኛሉ” ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት የኦፌኮ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጥሩነህ ገምታ ናቸው።
ፖሊስ ትናንት ሰላሳ አምስት ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የገለጸ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል የአቶ በቀለ ገርባ ሴት ልጅ የሆነችው እና ሹፌራቸው ከታሰሩት መካከል እንደሚገኙ አቶ ጥሩነህ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የፓርቲው ኃላፊ የሆኑት አቶ ጥሩነህ ጨምረውም በአሁኑ ጊዜ “በአጠቃላይ የታሰሩ ሰዎች ቁጥር 40 ነው” ብለዋል።
አቶ ጥሩነህ እንደተናገሩት በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሰዎች በተጨማሪ ትናንት ተከስቶ በነበረው ግጭት በመላው ኦሮሚያ የሞቱት ሰዎች ቁጥር የክልሉ መንግሥት ከሚለው በላይ መሆኑን የሚጠቁም መረጃ እንዳላቸው አመልክተዋል።