ሀ. የክልልነት ጥያቄ በኢትዮጲያ
በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ አመራር ኢትዮጵያ አስገራሚ የሚባሉ ስኬቶችን አስመዝግባለች።ፈታኝ የፖለቲካ ሂደቶችንም አስተናግዳለች።ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን በመጡበት ማግስት ጀምሮ ከማይረሱ ክስተቶች መከከል ከብዙ ውጣውረድ በሗላ የሲዳማ ሕዝብ የክልል ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱ ሊጠቅስ ይችላል።
የሲዳማ ዞን ወደ ክልልነት ማደግ ተከትሎ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የፖለቲካ እንቆቅልሽ እና ያለመረጋጋት ተከስቷል ።የደ/ብ/ብ/ሕ ክልል ዋና ከተማ የሆነችው ሐዋሳ የሲዳማ ክልል ልትሆን በሂደት ላይ ያለ ቢሆንም ሌሎች ዞኖችም ይህንኑ የአስተዳደር ከተማ የመምረጥ ስራ ላይ ይገኛሉ።ይህ የፖለቲካ ሂደት በደቡብ ክልል ጠረፍ ላይ ያለችውን ደቡብ ኦሞ ዞንን ከመጠን በላይ እንደሚጎዳት በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል።
በደቡብ ክልል ማእከላዊ መንግሥት ስር የምትገኘው ደቡብ ኦሞ፦ባላት ማህበራዊ ፥ኢኮኖሚያዊ፥ ባሀላዊ እና ታሪካዊ ሁለንተናዊ ፖለቲካዊ መስተጋብር የተነሳ በአለፉት ጊዚያቶች የክልልነት ጥያቄ ስታነሳ ቆይታለች።የኢፌዴሪ መንግሥት ግን እንደተለመደው የህዝቡን ጥየቄ ምላሽ ላለመስጠት ከጉዳዩ ጋር ምንም ተዛማጅነት የሌላቸውን ስብሰባዎችን ሲያካሔድና ጉዳዩን ሲያዘገየው ቆይቷል። መንግስት ሰላማዊ ከሚላቸው ዞኖች አንዷ ከሆነችው ደቡብ ክልል የሚነሱት ሰላማዊና ህገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ ውጤቱ የከፋ ይሆናል። ምክንያቱም በደቡብ ክልል ማዕከላዊ መንግሥት የመዘንጋት ስሜትና የባለቤትነት እጦት ምንአልባትም በቀጣይነት የተቃውሞ አመጽና ሁከት ሊፈጠር ይችላል ።ይህ ደግሞ ውጤቱ በሀገር ኢኮኖሚና እድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል ።
እንደሚታወቀው፣ አሁን ባለዉ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምክንያታዊ የሆነ ፖለቲካ ውይይት ቦታ አለዉ ብሎ መናገር አይቻልም።ምክንያታዊ በሆነ መልኩ፡ የተሻለና፡ ውጤታማ የመንግስት መዋቅር የመመስረት ጥያቄ፡ “ጠባብ ብሔርተኝነት” በሚል በፍጥነት ያስፈርጃል።ለሦስት አሠርት ዓመታት በህወሓት ሲመራ በነበረው፡ የኢህአዴግ መንግስት የክልል ጥያቄ ማንሳትን፡ “ኢትዮጵያን ለመከፋፍል መሞከር ነው” በማለት መፈረጅን እንደ ፋሽን ይቆጠር ነበር። ይህ አግባብነት ያለውና ምክንያታዊ የሆነ የሕዝብ ጥያቄን ላለመመለስ፡ እነደመሳሪያ ሲያገለግል የነበረ የፖለቲካ ስልት ነዉ። ከመጠኑ ያለፈ፡ ትልቅ የመንግስት አወቃቀርን ለመመስረት፡ በወኔ የሚንቀሳቀሱ ልሂቃን አሁንም ይህንን የፖለቲካ ስልት እየተጠቀሙበት እንደሆነ በግልጽ መታዘብ ይቻላል። በአካባቢው የነበሩ ታሪካዊ ፣ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዳራዎችን ችላ በማለት ፤ ግዙፍ ፣ሙሰኛና ውጤታማ ያልሆነ አስተዳደር ለመመስረት ይሞክራሉ። ይህ ያለፈበትና፡ ያረጀ የፖለቲካ ስልት ዉድቅ ተደርጎ፡ የሕዝብ ጥያቄንና አማራጭ የፖለቲካ ሃሳቦችን በሰለጠነና፤ ምክንያታዊ በሆነ በዉይይት የመመለስ ባህልን ፖለቲከኞችም ሆነ ማህበረሰቡ ማዳበር መቻል፡ አለባቸዉ።
በዚህ መንፈስ፡ ይህ አጭር ማስታወሻ፡ የኢትዮጵያ መንግስት የደቡብ ኦሞ ዞንን የክልልነት ጥያቄን በትዕቢት ችላ ብሎ ከሚያልፈው ይልቅ በአግባቡ እንዲመረምርና፡ አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጥ፡ ጥሪ ያቀርባል። የዞኗ የክልልነት ጥያቄ ለአመታት ለነገሰዉ ኢ-ፍታሐዊ ለሆነዉ የፖለቲካ ስርዓት እና የመገለል እርምጃ የተመዘነና፡ ተገቢ ምላሽ ነው ፡፡ አላማውም፡ ዘላቂና የተረጋጋ ብሔሮች፡ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳችዉን የሚያስተዳድሩበትን የክልል መንግስት መፍጠር ነዉ። ይህ ማስታወሻ፡ የዞንዋ የክልልነት ጥያቄ ከፌዴራል መንግሥት አዎንታዊ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት የሚያስረዱ፡ አምስት ዋና ዋና ምክንያቶችን ያብራራል።፡
- ከታሪክ አንጻር ደቡብ ኦሞ ክልል ነበረች
ደቡብ ኦሞ ከ1881ዓ.ም-1937 ዓ.ም ድረስ በማዕከላዊ መንግሰት ስር ትተዳደር ነበር ።ከ1938 ዓ.ም በኃላ ደቡብ ኦሞ በጋሞ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት ስር አንድ አውራጃ ሆና ነበር ።ይሁን እንጂ1980 ዓ.ም ጀምሮ የደቡብ ክልል እስከተመሰረተበት እና ክልል 10 ተብላ ተጠሪነቷ ለማዕከላዊ መንግስት ሆኖ ስትተዳደር ቆይታለች ፡፡ የደቡብ ኦሞ ያለፈው ታሪኳ ስታይ፡ አካባቢዋ ተጠሪነቷ ለማዕከላዊ መንግስት በነበረበት ጊዜ የተሻለ ልማት ሲታይ የነበር ስሆን በአንፃሩ በክልል መዋቅር ስር እንድትጠቃልል በተደረገበት ጊዜ ደግሞ በልማትና እድገቷ እየተጎዳች ለአስከፊ ድህነትና ኋላቀርነት ተዳርጋለች። የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 47(3)መሰረት ማንኛውም ብሔር ብሔረሰብ ወይም ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት እንደአለው ይደነግጋል ። በዚህ መሰረት በታሪክ የነበረ እና በህገ-መንግስቱ የተደነገገዉ የደቡብ ኦሞ ብሔር ብሔረሰብ ወይም ህዝብ የክልል የመመስረት ጥያቄ መብት ተመልሶ ሊሰጣቸዉ ይገባል ፡፡
2. ተደደጋጋሚ ና ውጤት አልባ የመንግስት መዋቅር ለዉጦች
ደቡብ ኦሞ ዞን የጋሞ ጎፋ ክልል አካል በነበረችበት ጊዜ ፣ ለአርባምንጭ ከተማ እና አካባቢዋ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክታለች። በተካሄደው መልሶ ማዋቀር መሠረት የደቡብ ክልል አካል በሆነችበት፡ ጊዜ፡ ለአርባምንጭ ከተማ ልማት ያደረገችው የመዋዕለ ንዋይ አስተዋጽኦ ዕውቅና አላገኘም። እንደዚሁ ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት ለሐዋሳ ከተማና አከባቢዋ ልማት እና ብልጽግና አስተዋጽኦ ስታደርግ ቆይታ ባዶ እጇን ልትሸኝ ተቃርባለች፡፡
ሀዋሳ የደቡብ ክልል ዋና መስተዳድር እንደመሆኗ ለደቡብ ኦሞ ህዝቦች ለአስርተ ዓመታት የተስፋ እና የአንድነት ምልክት ሆና ቆይታለች፡፡ከተማዋ ለሲዳማ ዞን መስተዳድር መሰጠቷን ተከትሎ ደቡብ ኦሞ እንደገና ለአስርተ ዓመታት ያስመዘገበችውን ተስፋዋንና፡ እና በዋናነት የመሠረተ ልማት አውታሮችን ለማጣት ተቃርባለች።
በእነዚህ ተደደጋጋሚ የመንግስት መዋቅር ለዉጦች፥መሠረተ ሀብቶች ሁሉ የክልሉን ዋና ከተማ ለመገንባት ስለተመደቡ፥የደቡብ ኦሞ አስተዳደር ዋና ከተማ የሆነችው ጂንካ ከባድ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ደርሶባታል ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ፣ የቴክኒክ ማሠልጠኛ ተቋማት ፣ የክልል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ፣ የግል ኢንቨስትመንቶች በእነዚያ ከተሞች ውስጥ ተከማችተው ነበር ፡፡የደቡብ ኦሞ ህዝቦች ታሪካዊ እና ህገ-መንግስታዊ የራስን አስተዳደር እና ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናን የሚነፍግ ና ውጤት አልባ የመንግስት መዋቅር ለዉጦች ዉስጥ፡ የመኖር ፍላጎትም ሆነ ትዕግስት የላቸዉም። አሁን የሕዝቡ ብቸኛ ፍላጎት ዘላቂነት ባለዉ ክልል መደራጀት ብቻ ነዉ።
3. ከለሌሎች፡ የደቡብ ብሔርና፡ ብሔረሰቦች ጋር ጠንካራ የባህልና የስነልቦና ትሥስር የለሌው መሆኑ
የደቡብ ኦሞ ዞን ብሔረሰቦች በአቅራብያ ካሉት፡ ለምሳሌ፡ ከጋሞ፣ ከጎፋ፡ ከኮንሶ ጋር በባህልና በቋንቋ የማይገናኙ ናቸው። እንዲሁም ከእነዚህ ጎረቤታማ ብሄረሰቦች ጋር የጋራ ባህላዊ ውርስ እና ተመሳሳይ የአስተሳሰብ አካሄድም የላቸውም። በ ኢኮኖሚያዊ ልማት ረገድ ፣ ደቡብ ኦሞ አሁንም ወደ ኋላ ከቀሩት ቀጠናዎች አንዱ ነው ፡፡የደቡብ ኦሞ ህዝብ፥ በቋንቋ ፣ በባህል ፣ በሥነልቦናዊ አካሄድ ፣ እና በኢኮኖሚያዊ ልማት ደረጃ ከፍተኛ ልዩነት ያላቸውን ሕዝቦች በአንድ ክልል ማዋቀር ትክክል አይደለም ብለው ያምናሉ።ምክንያቱም ቀድመው የለሙት አካባቢዎች፡ የበለጠ ተጠቃሚ ይሆኑና የደቡብ ኦሞ ሕዝብ ከበፊቱም ለባሰ ኋላቀርነት ይዳረጋል። አሁን ያለው የመንግስት መዋቅር በመሠረተ ልማት እና በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ልማት ያለውን ልዩነት በከፍተኛ ደረጃ ሊያባብሰዉ ይችላል።
4. ራስን በራስ የማስተዳደር ጠንካራ አቅም
የደቡብ ኦሞ ዞን ማዕድናት ፣ የግብርና እና የግጦሽ መሬቶች ፣ የውሃ ሀብቶች ፣ ደኖች ፣ብሔራዊ ፓርኮች ፣ የዓሳ ሀብት እና የወጣት የሰው ኃይልን ጨምሮ ከፍተኛ፡ የተፈጥሮ ሀብቶች አሏት ፡፡ ዞኗ በአገሪቱ ከሚገኙት ከፍተኛ የቱሪስት መዳረሻዎች አንዷነች ፡፡ እነዚህን የምጣኔ፡ ሀብቶች፡ ለአካባቢውና እና ለብሔራዊ ልማት እና ብልጽግና በውጤታማ እና ዘላቂ መልክ ለመጠቀም፡ ራስን በራስ ማስተዳደርና፡ የብሔር ብሔረሰቦች፡ ተሳትፎ፡ ከፍተኛ ሚና፡ አለው።ደቡብ ኦሞ ህዝብ በክልል የመደራጀት መብት ተጠቃሚ የሚደረግ ከሆነ የክልልነት መብቷን ብታገኝ ከላይ የተጠቀሱትን ሀብቶች ከብልሹ አሰራርና፡ ከብክነት ነጻ በፀዳ የሆነ፡ መልኩ ለማስተዳደርም ሆነ ለመጠቀም ያስችለዋል፡፡
የደቡብ ኦሞ ዞን ከህዝብ ብዛት (ከ 1 ሚልየን በላይ) ፣ ከተፈጥሮ ሀብቶች ፣ ከአርበኝነትና እና
የኢትዮጵያዊነት ስሜት፣ በሰላም አብሮ የመኖር ታሪክ፣ከአካባቢያዊ እና ለአገራዊ ልማት ቁርጠኝነት፡ አንጻር፡ ከሌሎች፡ አከባቢዎች ስትነጻጸር የተሻለ ደረጃ ላይ መሆኗን በመገንዘብ፡ መንግስት፡ የክልልነት መብቷን፡ ማክበር እና ማስከበር አለበት፡፡
- የመሠረተ ልማትና የተጓዳኝ አገልግሎቶች አግባብ ያልሆነ ክፍፍል
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ለመግባት ነጥብ ያነሳቸው፣ ትምህርት ያቋረጡና በሙያ መሰልጠን ለሚፈልጉ ወጣቶች ልዩ ልዩ ስልጠና መስጫ ተቋማት ባለመኖራቸው የወጣት ሥራ አጥነት በአስጊ ደረጃ፡ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በየተቋማቱ የስራ ማስታውቂያ ሲወጣ በአብዛኛው አመልካቾችና ተቀጣሪዎች ከሌላ ቦታ የሚመጡ እንጂ ከአካባቢው የሚወጡ አይደሉም:: ይሕ የሚሆንበት ምክንያት የአከባቢው ወጣቶች በዕውቀትና ክህሎት ዕጥረት የውድድር መስፈርቶችን ማሟላት ስለማይችሉ ነዉ፡፡ ከላይ የተጠቀሱት፡ ዞኗ ውስጥ ከሚታየው የመሰረተ ልማትና የሕዝብ አገልግሎቶች እጥረት በተጨማሪ ነው። ሰለዚህ ሕዝቡ በክልል ተደራጅቶ የሥልጠና ተቋማትን በመክፈት የወጣት ሥራ አጥነትን መቀነስ ይፈልጋል ፡፡
ሓ. ግልፅ እና ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲካሄድ ጥሪ
የደቡብ ኦሞ ህዝቦች በክልል የመደራጀት ጥያቄ ተደባብሶና ተሸፋፍኖ ሊቀር አይችልም፡፡ ጥያቄው የወጣቱ ትውልድ ነው። በደቡብ ክልል ውስጥ የወደፊቱን ፖለቲካን ሁኔታ ሊወስን ይችላል። የሕዝቡ ጥያቄ፡ ራስን በራስ ከማስተዳደር መብት አንፃር ብቻ ሳይሆን በተቀላጠፈ መልኩ የተፈጥሮ ሀብትን ከመምራት ፣ ከመልካም አስተዳደርን እና ከዴሞክራሲ አኳያም ስታይ፡ አግባብነት ያለዉ ጥያቄ ነው ፡፡ በመጠን አነስተኛ አከባቢያዊ፡ መንግስታት (small local governments) ሀብታቸውን በተሻለ ሁኔታ እንደሚያስተዳድሩ በሌሎች አገሮች የታየ ነው፡፡ በተጨማሪም ሙስናን በመዋጋትና፡ በአደጋና፤ ወረረሽኝ ጊዜም ቀልጣፋና፡ ውጤታማ ምላሽ እነደሚሰጡ ይታወቃል፡፡
የደቡብ ኦሞ ዞን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች፡ በሠላምና፡ በመከባበር የሚኖሩበት ብቸኛዋ
የኢትዮጵያ ዞን ነች ማለት ይቻላል። ከጎረቤት አካባቢዎችና ብሔረሰቦች ጋር የረጅም ጊዜ ወዳጅነት አላት ፡፡ ዞኗ በመጪዎቹ ምዕተ ዓመታት ዘመናዊዉን ኢትዮጵያ ትወክላለች ፡፡ “ልዩነታችን አንድነታችን” ነዉ የሚለውን አባባል ደቡብ ኦሞ እውን ታደርጋለች። ነገር ግን ይህ ሁሉ ሊሆን የሚችለዉ ብሄሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን የማስተዳደር እና የመበልጽፀግ ታሪካዊ እና ህገ-መንግስታዊ መብታቸው ሲከበር ብቻ ነዉ፡፡ የደቡብ ኦሞ ዞነን የክልልነት፡ ጥያቄ ለኢትዮጵያና፡ ለዞኗ ሕዝቦች፡ የተሻለ፡ ጥቅም ሲባል አሁኑ አዎንታዊ ምላሽ ሊሰጠዉ ይገባል፡፡
ዶክተር አስረስ አድሚ ጊካይ (ፒ.ኤች.ዲ)
ሌክቸረር (ብሩነል ዩኒቨርሲቲ ለንደን, እንግሊዝ)