«ሕወሓት ዘመኑ ከሚፈልገው ለውጥ ጋር ለመሄድ ፍላጎት አለማሳየቱ እንድለቅ አስገድዶኛል» የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣን

ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ /ሕወሓት/ የትግራይን ሕዝብ ከልማትና ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ወደኋላ ያስቀረ ፓርቲ መሆኑን ከድርጅቱ ራሳቸውን በፈቃዳቸው ያገለሉ አንድ የቀድሞ ከፍተኛ አመራር ገለፁ። በሕወሓት ድርጅትና በቀድሞ የኢህ አዲግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉት አቶ ሚልዮን አብርሃ ለዶይቼ ቨለ “DW” እንደተናገሩት ድርጅቱ ለሀሳብ ልዩነት ቦታ አለመስጠቱ ፣ የተሻለ ሀሳብ ያለውን አመራር አለማስተናገዱና ዘመኑ ከሚፈልገው ለውጥ ጋር ለመሄድ ፍላጎት አለማሳየቱ ከሕወሓት አመራርነት በፈቃዳቸው ለመልቀቃቸው ዋንኛ ምክንያቶች ናቸው። ድርጅቱ የክልሉ ሕዝብ የሚያነሳቸውን ተደጋጋሚ የልማት፣ የመብት መከበርና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለማዘናጋትና ለማፈን እንዲሁም የአንድ ፓርቲ አምልኮ እንዲኖር የትግራይን ሕዝብ ከጎረቤት ሀገርና ከሌላውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በሰላምና በፍቅር እንዳይኖር የግጭትና የጥላቻ አደገኛ ፕሮፓጋንዳን መንዛት የማታገያ ስልቱ አድርጓል ሲሉም ወቅሰዋል። ሕዝቡ ለውጥ ፈላጊ በመሆኑ የሌሎች ወገኖቹን ድጋፍ ካገኘ ሕወሓትን ወደ ትክክለኛ መስመር መመለስ ካልሆነም ማክሰም እንደሚችልም ነው የገለፁት።

የሕወሓት ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ሚሊዮን አብርሃ ለበርካታ ዓመታት በድርጅቱ ውስጥ በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉ ሲሆን በቀድሞው የኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት የገጠር ፖለቲካ ዘርፍ የቢሮ ኃላፊ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የኢህአዴግ ተወካይ፣ እንዲሁም የኢህአዲግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ቢሮ ኃላፊ በመሆን ለረጅም ጊዜያት መስራታቸውም ይጠቀሳል። “ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ /ሕወሓት/ ከምስረታው ጀምሮ የተሻለ ሀሳብ ይዞ የሚመጣን አመራር የማግለልና ወደኋላ የማስቀረት አባዜ የተጠናወተው በመሆኑ በርካታ አገርን መለወጥ የሚችሉና በትግሉ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የነበራቸው ወጣቶች ከድርጅቱ በተለያዩ ጊዜያት እየለቀቁ ለመውጣት ተገደዋል የሚሉት አቶ ሚልዮን ድርጅቱ ለሀሳብ ልዩነት ቦታ አለመስጠቱ ፣ የተሻለ ሀሳብ ያለውን አመራር አለማስተናገዱና ዘመኑ ከሚፈልገው ለውጥ ጋር ለመሄድ ፍላጎት አለመኖሩ ከሕወሓት አመራርነት በፈቃዳቸው ለመልቀቃቸው ዋንኛ ምክንያቶች መሆናቸውንም በተለይ ለዶይቼ ቨለ “DW“ ገልፀዋል::በየትኛውም የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ተመሣሣይ አስተሳሰብ የማራመድ ግዴታ ባይጣልም ሕወሓት ግን የድርጅቱ አባላት በሙሉ በጥቂት ግለሰቦች አመለካከት፣ አስተሳሰብና ፍላጎት ብቻ እንዲመሩ ተፅዕኖ ሲያደርግ መቆየቱንም አቶ ሚልዮን ጠቅሰዋል:: የክልሉ ሕዝብ በርካታ የልማት፣ የመብት መከበርና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ቢኖሩትም እነዚህን ችግሮች ከመፍታት ይልቅ አመራሩ በሀሳብ ልዩነት ሳይሆን በጭቅጭቅና በሹኩቻ ተጠምዶ የትግራይን ሕዝብ ከልማትና ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ወደኋላ እያስቀረና የስልጣን እድሜውንም ለማርዘም የብሽሽቅ ፖለቲካን ዋና የመታጋያ ስልቱ አድርጎ ሕዝቡ ሌሎች ወንድሞቹን እንዲጠላ እያደረገ ነው ብለዋል። በተለይም የፌደራል መንግሥት የሚመድብለትን ዓመታዊ በጀት የክልሉን ኢኮኖሚ ከመገንባት ይልቅ ለልዩ ሚሊሻ ስልጠናና ለወታደራዊ ቁሳቁሶች ግዢ እያባከነው መሆኑንም ነው ያስረዱት:: በድርጅቱ ስም እየተንቀሳቀሱ ያሉ ጥቂት ግለሰቦችም በክልሉ ውስጥ የሚነሳውን ተደጋጋሚ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለማዘናጋትና ለማፈን እንዲሁም የትግራይ ሕዝብ ከጎረቤት ሀገርና ከሌላውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በነፃነትና በትብብር እንዳይሰራ እያደረጉት ይገኛሉ ሲሉ ወቅሰዋል።ሕወሓት የግንባር ድርጅቱ ኢህአዲግ ፓርቲዎችና የአጋር ድርጅቶች መሰረታዊ ችግሮቻቸውን በግልፅ ከፈተሹበትና ከገመገሙበት ከጥልቅ ተሃድሶው መድረክ በኋላም እንኳ ልዩነቶችን በሰላማዊና በአሳማኝ ሁኔታ መፍታት እንዲሁም በሀሳብ ማሸነፍ የሚቻልበትን የፖለቲካ ምህዳር አጥብቧል ብለዋል አቶ ሚልዮን። ከዚህ ሌላ እንኳንስ ተፎካካሪዎች የሕወሓት አባላቶችም የሃሳብ ልዩነታችንን በነፃነት እንዳንገልፅ በአመራሩ በታፈንበት ሁኔታ፣ በትግራይ የፖለቲካ ምህዳሩ በጠበበትና የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችና አባላት በክልሉ መንግስት ተፅዕኖ ስር በወደቁበት በተለይም በኮረና ምክንያት ዓላማና ፕሮግራማቸውን ማስተዋወቅ በማይችሉበት በአሁኑ ጊዜ የክልሉን በጀት አባክኖ ቅቡልነት የሌለው ምርጫ አካሂዳለሁ ማለት ተገቢ አይደለም ሲሉም ተችተዋል:: ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ የተለያዩ መሆናቸው አፅንዖት ሊሰጠው ይገባል የሚሉት የቀድሞ የሕወሓት ከፍተኛ አመራር አቶ ሚሊዮን አብርሃ የትግራይ ሕዝብ ለውጥ ፈላጊ በመሆኑ ከኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ድጋፍ ከተደረገለት ሕወሓትን ወደ ትክክለኛ መስመር መመለስ ካልሆነም ማክሰም እንደሚችልም አስታውቀዋል። የትግራይ ሕዝብ በተለይ ወጣቱ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚሰነዘርንን አደገኛ ፕሮፓጋንዳ እየሰማ ከሰላምና ልማት ይልቅ አውዳሚ ጦርነት ናፋቂ እንዳይሆንም ጥሪ አቅርበዋል።

Share this post