አምቦ ዩኒቨርሲቲ የባህል ጥናትና ምርምር ማዕከል ያቋቋመለት ታላቁ ጸሐፌ ተውኔት ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድኅን ስለ ሕይወት ታሪኩ ራሱ ከጻፈውና ሌሎችም ከመዘገቡት ማስረጃዎች ለመረዳት እንደሚቻለው በ1929 ዓ፡ ም የተወለደው የሜጫ ጎሳ አባል ከሆኑት ከአባቱ ከሐምሳ አለቃ ገብረ መድኅን ሮባ ቀዌሳ እና የጠራ ምድር አማራ ከነበሩት እናቱ ከወይዘሮ ፈለቀች ዳኘ ነው፡፡ የተወለደበት ቦታ ፡በቀድሞ አጠራሩ በጅባትና ሜጫ አውራጃ ፤ ከአምቦ ከተማ 30 ኪሎሜትር ርቃ በምትገኝና ቦዳ አቦ ተብላ በምትጠራና ተራራ ሥር በምትገኝ ትንሽየ የገጠር ከተማ ነው፤፤በዚህች መንደር ታዋቂው የጦር ሰው፤መለኛውና ፖለቲከኛው ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ መወለዳቸው ይታወቃል፡፡ሎሬት ጸጋየ እንደሚለው( እሳትና ውኃ 2010፤3) በልጅ ኢያሱ ጊዜ የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ጦር ንጉሥ ሚካኤልን ለማገድ ሲሄድ በምኒልክ ግቢ የእልፍኝ አሽከር የነበሩት አባቱ ሐምሳ አለቃ ገብረ መድኅን ከጦሩ ጋር ነበሩ፡፡ያኔ የአንኮበር ከተማ በጦርነት ሲቃጠል በጊዜው ቤት ንብረታቸው የተቃጠለባቸው ሰዎች ለጥበቃ ለየትልልቁ ሰው ተከፋፍለው ሲሰጡ የእርሱ እናት ቤተ ሰቦችም በአባቱ ጥበቃ ሥር ውለው ከአንኮበር ይወጣሉ፡፡
ከጊዜ በኋላ የቤተ መንግሥት የግቢ ሚኒስትር የነበሩት ዘመዱ ፊታውራሪ ኢብሳ የጸጋየን ሴት አያት ልጅሽን ፈለቀችን ለወንድሜ ለአምሳ አለቃ ገብረ መድኅን ዳሪለት ብለው ስምምነት ከተደረገ በኋላ እናቱ በ13 ዓመታቸው አባቱን ያገባሉ፡፡ጸጋየ ከመውለዱ በፊትም ወላጅ አባቱ የኢጣሊያ ጦር እየገፋ በመምጣቱ ወደ ማይጨው ይዘምታሉ፡፡በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተመራው የኢትዮጵያ ጦር ድል ሳይቀናው ቀርቶ ማይጨው ላይ እንደተፈታና ወላጅ አባቱም ገና ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ በፊት ጣሊያን በባንዳ ሰላዮቹ አማካይነት የዐርበኞችን ቤት እያሰለለ ማቃጠል ፤ንብረታቸውን መዝረፍና ቤተሰባቸውን ማሳደድ ሲጀምር ሕፃኑ ጸጋየ ገና አራስ ቤት እያለ ቤታቸው እዚያው ቦዳ ውስጥ በባንዳዎች ተቃጠለ፡፡እናቱ ወይዘሮ ፈለቀች ቤታቸው ሲቃጠል አራስ ልጃቸውን ወደ ጓ,ሮ በመውሰድ ከባሕር ዛፍ ጀርባ በአገልግል ውስጥ አድርገው ከደበቁት በኋላ ከባንዳዎች ጋር መታኮስ ይጀምራሉ፡፡የባንዳው ጦር በርትቶ ጨርሶ ሊደመስሳቸው ሲል የአባቱ ባልደረቦች ደርሰው ነፍሳቸውን ያተርፏቸዋል፡፡ ከሞት እንደተረፉ ወላጅ እናቱ ጸጋየን ይዘው ወደ አያት ቅድመ አያቶቻቸው ቀየ ወደ ጎረምቲ ይሰደዳሉ፡፡በኋላ ቤታቸውን ያቃጠለባቸውን ሰው ለመፋረድ ቤተ ሰቦቹ ለዳኞች አቤቱታ ቢያቀርቡም ጉቦ የለመዱት ዳኞች ሳይፈጽሙላቸው ይቀራሉ፡፡
ሲሰደዱ በደንዲ ሐይቅ ዳርቻ በኩል ነበርና ልክ እንደ እሳቱ ሁሉ በልጅነቱ ያየው የውኃው ነጸብራቅ ከአእምሮው ውስጥ ሳይጠፋ ኖሯል፡፡እንግዲህ ቤተሰቦቹን ከአንኮበር ያሰደዳቸው እሳት እሰከ ቦዳ አቦ ድረስ ተከትሎና ሕጻኑን ጸጋየንም የሰለባው አንድ አካል አድርጎ አሰቃያቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በሰውነቱ ላይ የእሳት ቃጠሎ ሠረፀ፡፡ ሎሬቱ እሳት ወይ አበባ የሚል የግጥም ትሩፋቱን ትቶልን የሄደው፡ ከዚሁ የተነሣ ይመስላል፡፡በዚህም በልጅነቱ ከአባቱ ወገኖች ኦሮሚፋን፤ከእናቱ ቤተሰቦች ደግሞ አማርኛን፤ግእዝን፤ሥነ፡ግጥምንና፡ቅኔን ተምሯል፤ አለቃ ብሥራትና አባ ወልደ ማርያም በተባሉ መምህራን አማካይነት ዳዊት ደግሟል፡፡በመሆኑም የሁለት ባህሎች ውጤት አካል ሆኖ ያደገው ጸጋየ ከነጻነት በኋላ አምቦ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቶ ሲማር ትምህርቱ በቀላሉ ይገባው ጀመር፡፡ጎበዝ ተማሪ ከመሆኑም ባሻገር ገና በ13 ዓመቱ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፤ ወላጆችና የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ በተገኙበት ግፍ የተሞላውን የዲዮኒሰስ የዳኝነት ሥራ መነሻ አድርጎና የዳኞችን አድላዊነት የሚያመለክት ቴአትር ደርሶ ባቀረበ ጊዜ ተወዳጅነትን አግኝቷል፡፡ሥራውም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በጊዜው ታትሞለታል፡፤
የአንደኛና የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአምቦ ከተማ ያጠናቀቀው ጸጋየ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አበባ በጀኔራል ዊንጌትና በንግድ ሥራ ትምህርት ቤቶች አጠናቅቋል፡፡ በሕግ የኤል ኤል ቢ ዲግሪውን ከአሜሪካ፤ ቺጋጎ ከብላክ- ስቶን የሕግ ትምህርት ቤት የተቀበለ ሲሆን በ29 ዓመቱ በሥነ ጽሑፍ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እጅ ሽልማት ወስዷል፡፡ በተለይም የግጥሙን የሐሳብ ጥልቀት ለመረዳት ብዕረ ከባድ የሆነው ሎሬት ጸጋየ በቁጥር ከ30 በላይ የሆኑ ቴአትሮችን በአማርኛም ፤በእንግሊዝኛም ደርሶና ከውጭ ቋንቋ ተርጉሞ ለኢትዮጵያውያንና ለውጭ አገር ተመልካቾች አሳይቷል፡፡በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ቴአትር ቤቶችን በዲሬክተርነት መርቷል‹‹ ቤተ ቴአትር መሥርቷል፡፡በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሠርቷል፡፡በባህሉ ዘርፍ በምክትል ሚኒስትርነት ሀገሩን አገልግሏል፡፤በሙያው በአፍሪካና በተቀረው ዓለም የታወቀ ሲሆን የቴአትርና የጥናት ዝግጅቱን በሴኔጋል፤በናይጀሪያ፤ በግብጽና በሌሎች አገሮች አቅርቧል፡፡
የእንግሊዝን፤ የፈረንሳይን፤ የሮምንና የሌሎች አገሮችን የቴአትርና የድራማ ጥበብ ተዘዋውሮ መቅሰሙና፤በልዩ ልዩ ሀገራት ጥበባዊ ጉዞ ማድረጉ፤ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤የሳይንስና የባህል ድርጅት የነጻ ትምህርት እድል አግኝቶ የቴአትር ሙያን በተግባር ማጥናቱ፤እኤአ በ1960 ዎቹ ላይ በተባበሩት መንግሥታትና በአፍሪካ አንድነት ድርጅቶች አስተባባሪነት በዳካር በተከናወነው የአፍሪካ የባህልና የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል ላይ ስለኢትዮጵያና ስለ ግብጽ፤ ስለ ሌሎችም ጥቁር ሕዝቦች የቴአትር ጥበብ ጥናትና ምርምሩን፡ማቅረቡና፡ኦዳ፡ኦክኦራክል፡የተሰኘ፡ቴአትሩን፡በእንግሊዝ፤በዴንማርክ፤በኢጣሊያ፤በሩማኒያ፤በታንዛኒያ፤በናይጀሪያ፤ በኬንያና በአሜሪካ ማቅረቡ በሙያው የገዘፈና ዝነኛ እንዲሆንና ከተለያዩ ዓለማት ልዩ ልዩ የእውቅናና የኖቤል ሽልማት እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡
ክብረ አፍሪካ በሚል ከአፍሪካ ዘመን አይሽሬ ባህል በፊት ስለነበረው ጥበብ ጥልቅ ጥናትና ምርምር ከማድረግ አልፎ አፍሪካ የጥንታዊቱ ግሪክ ቴአትር ጀማሪ መሆኗን አረጋግጦዋል፡፡የሥነ ሰብእ (አንትሮፖሎጂ) ጥናት ተመራማሪ፤ ሐያሲ፤ዲሬክተር፤ ባለቅኔ፤ጸሐፌ ተውኔት፤—- የሆነው ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድኅን ከሠራቸው ሥራዎቹ ውስጥ ለአብነት እንደነ ኦቴሎ፤ማክቤዝ፤ሐምሌት፤የመሳሰሉትን የሼክስፒር ሥራዎች፤እንደዚሁም ከሞሌር ሥራ ውስጥ ታርቱፍና ዶክተር ለራሴ የመሳሰሉትን በተመጣጣኝ ክላሲክ ቋንቋ በመተርጎም አማርኛ ከዓለም ታላላቅ ቋንቋዎች ጋር የሚመጣጠን መሆኑን ያስመሠከረና የግእዝን ባለጸጋነት በግጥሞቹ ተጠቅሞ ያረጋገጠ ታላቅ ጠቢብ ነው፡፡ በሥነ ጥበቡ ዓለም ልዕለ ጠቢባን መሆኑን የተረዱት እንደነ ሊዎፖልድ ሴዳር ሴንጎር፤እንደነ ዶናልድ ሌቪን ፤እና እንደነ ሩዶልፍ ሞልቬር የመሳሰሉትና ሌሎችም ለኢትዮጵያዊው የብዕር ዐርበኛ ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድኅን ከፍተኛ የሆነ አድናቆትና አክብሮት የሰጡት ከበለጸገ ችሎታው የተነሣ ነው፡፡
ከሎሬት ጸጋየ ሌሎች ሥራዎች ውስጥ የከርሞ ሰው፤የእሾህ አክሊል፤ ጀሮ ደግፍ፤የደም አዝመራ—ሲጠቀሱ በአብዮቱ ዘመን ሀሁ በስድስት ወር፤እናት ዓለም ጠኑ፤መልእክተ ወዛደር፤ሀሁ ወይም ፐፑ፤አቡጊዳ ቀዊሶ—የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡በግጥም ደረጃ ዐድዋ፤ ቴዎድሮስ፤አይ መርካቶ፤አዋሽ፤ ይድረስ ለእኛ፤ እሳት ወይ አበባና ሌሎች ስፍር ቁጥር የሌላቸውና የሚያስደምሙ፤ የሚያስደንቁ፤ የሚያመራምሩና የሀገር ፍቅር ስሜትን እንደ ቤንዚን የሚያቀጣጥሉ ሌሎች ግጥሞቹ ይጠቀሳሉ፡፡በአማርኛና በእንግሊዝኛ ይጽፍ የነበረው ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድኅን ኒውዮርክ ውስጥ በሕክምና ላይ እንዳለ ያረፈው ፌብሩዋሪ 25 ቀን 2006 ሲሆን ዐፅሙም በክብር ያረፈው በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ውስጥ ነው፡፡ በመሆኑም ስለሚወድዳት ሀገሩ ኢትዮጵያና ሕዝቧ የሠራው ሕያው ሥራ ለዘለዓለም ሲዘከር እንዲኖር አስችሎታል፡፡
ውድ ታደለ፣
አንዳንድ ነገሮችን ግልጽ ማድረግ ይኖርብሃል።
1/ ጸገመ “እሳትና ውሃ” የሚል ጽፎአል?
2/ “በልጅነቱ ከአባቱ ወገኖች ኦሮሚፋን፤ ከእናቱ ቤተሰቦች ደግሞ አማርኛን፤ ግእዝን፤ ሥነ፡ግጥምንና፡ ቅኔን ተምሯል” ያልከው ትንሽ የተዛነፈ ይመስላል። ከኦሮሚፋ ቋንቋውን ብቻ እንጂ ሌላ እንዳልተማረ አስመሰልከው፤ አገላለጽህ ይሆናል እንጂ አስበህ አይመስለኝም። ቴአትሩንና ቅኔዎቹን (እሳት ወይ አበባ) ያደመጠ ማክማክሳውን፣ ጌሬርሳውን፣ ወዘተ ምንኛ እንደ ተካነው ግልጽ ነው። አንድ ወዳጄ ቅርብ ጊዜ አንድ የቪዲዮ ቁራጭ ልኮልኝ ጸገመ አምቦ ላይ ይመስለኛል በኦሮምኛ ሲጨፍር አይቼአለሁ።
3/ “በሥነ ጥበቡ ዓለም ልዕለ ጠቢባን መሆኑን የተረዱት እንደነ ሊዎፖልድ ሴዳር ሴንጎር፤እንደነ ዶናልድ ሌቪን ፤እና እንደነ ሩዶልፍ ሞልቬር የመሳሰሉትና ሌሎችም ለኢትዮጵያዊው የብዕር ዐርበኛ ሎሬት ጸጋየ ገብረ መድኅን ከፍተኛ የሆነ አድናቆትና አክብሮት የሰጡት ከበለጸገ ችሎታው የተነሣ ነው።” ትክክለኛ አባባል ነው፤ ሆኖም በእንግሊዝኛ መጻፍ ጀምሮ (Oda Oak Oracle) ያን ጥሎ ሙሉ በሙሉ በአማርኛ መጻፉ በውጭው ዓለም ዘንድ ከመታወቅ ይልቅ የአገሬውን ማጎልበት ዓላማው እንዳደረገ ግልጽ ነው። አንተም እንደ ገለጽከው በአገሩ የሚገባውን ክብር አላገኘም። በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ማእከል መቋቋሙ ይልቅ ትልቅ ተስፋ ሰጭ ነው።